ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አሜሪካን ተጠያቂ አደረጉ

ታትሟል

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራ 31ኛው የነጻነት በዓልን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ለሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።

በእርሳቸው አገላለጽ፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ "በአሜሪካ የሚመራው የምዕራባውያን ኃይል፣ የአሜሪካ ሕዝብንም ይሁን የምዕራቡ ዓለምን የማይወክል አደገኛ አካሄድ ጀምሯል።"

"ዓለም የኛ ይሆናል፣ በሁሉም ዘርፍ ያለን ኃያልነት ተገዳዳሪ አይኖረውም" ብለው ምዕራባውያኑ እንደተነሱ ጠቅሰው በዚህም ኤርትራ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ከመተቸት አልፈው ለሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አሜሪካን ተጠያቂ እስከማድረግ ደርሰዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ውይይት ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ ማዕቀቦች እንዲጣሉ የተነሱ ሐሳቦችን ከተቃወሙ አገራት አንዷ ኤርትራ እንደሆነች አይዘነጋም።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባደረጉት ንግግር በዋነኛነት አሜሪካ ሊገዳደሯት የሚችሉ ኃይሎች ላይ "የአፈና ፖሊስ" እንደምትከተልና፣ ይህንን ፖሊሲዋን ሩሲያን "ለመቆጣጠር" እንዳዋለችው ጠቅሰዋል።

የሩሲያ የቅርብ ጎረቤቶች የሆኑ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት "እንደ እጅ አዙር መጠቀሚያ" እንደዋሉ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ይህ "የአፈና ፖሊሲ" እንደሆነ ገልጸው፣ የዩክሬን ሕዝብ የዚህ ሰለባ ሆኗል ሲሉ ተችተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ባለፉት 30 ዓመታት ይህ አካሄድ "አልሠራም" ሲሉም አክለዋል።

"ማስፋራራት፣ መቅጣት፣ መውረር፣ ስም ማጠልሸት፣ ማዕቀብ መጣል፣ ሰብአዊ መብትን እንደ መሣሪያ መጠቀም አልሠራም።"

በእጅ አዙር የምጣኔ ሀብት ጫና ለማሳደር ከሩሲያ በተጨማሪ ቻይና ላይም "እንደተቃጣ" ገልጸዋል።

"ታይዋን እና ሆንግ ኮንግን እንዲሁም በአጠቃላይ እስያ ያሉ አገራትን እንደ መሣሪያ ለመጠቀም ተሞክሯል። ይህም ከሩሲያ ቢበልጥ እንጂ የማይተናነስ ቀውስ ያስከትላል።"

ጠቅለል አድርገውም ዓለም አቀፍ ሕግጋት የሚከበሩበት፣ ማዕቀቦች የሚቀለበሱበት፣ ዓለም አቀፍ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚረጋገጥበት፣ ሉዓላዊ አገሮች የማይገረሰሱበት እንዲሁም አገራዊ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ ትብብር የሚደረጅበት ዓለም መገንባትን እንደ አማራጭ አቅርበዋል።የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለኤርትራ 31ኛው የነጻነት በዓል ባደረጉት ንግግር፣ የአፍሪካ ቀንድን "መረጋጋት ማረጋጋጥ" የኤርትራ አገረ ግንባታ ዋነኛ ማጠንጠኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

በንግግራቸው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት፣ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እንዲሁም "የምዕራባውያን ጫና" ይገኙበታል።

"የቀጠናውን መረጋጋት ማስጠበቅ፣ የጋራ ትብብርን ማጠናከር እና በሉዓላዊ አገራት መካከል ትስስርና እድገትን ማረጋገጥ የአገር ግንባታው ዋነኛ ማጠንጠኛ ነው፣ ሆኖም ይቀጥል" ብለዋል።

"የውስጥ እና የውጭ አፍራሽ አጀንዳዎች" ባሏቸው ጉዳዮች "የጎረቤት አገራት ዜጎች" እንደሚፈተኑም አያይዘው ጠቅሰዋል።

ከቀጠናው ባለፈ አፍሪካን እንደ አህጉር ቀጠናዊ ትስስሮችን ማጠናከር እንዳለባት ጠቅሰው "ይህ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን እጅግ አስፈላጊ ነው" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተውታል።

የኤርትራ መንግሥት "ለቀጠናዊ ትስስር ግብዓት እንዳፈሰሰ" ከዚህ ባሻገርም ለጋራ የምጣኔ ሀብት እድገት፣ ለጸረ ሽብር ትግል እና ብሔራዊ ደኅንነት ስጋትን ለመቀልበስም "እንደሚታጋ" ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ለ30 ዓመታት የተካሄደውን የትጥቅ ትግል የመራው የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር (ሻዕቢያ) የኤርትራ መዲና አሥመራን የተቆጣጠረበት ቀን በኤርትራ ተከብሮ ውሏል።

የነጻነት ቀንን አስመልክተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ በዓሉ የአገሪቱ "አሁናዊ፣ የቀድሞ እና የወደፊት ሁኔታ የሚቃኝበት" ብለውታል።

በቀጠናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ "ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት" የኤርትራን ሉዓላዊነት እና ነጻነት ለመጠበቅ የተደረገው ትግል አልፎም አገሪቱ ለወደፊት ማሳካት የምትሻው የሚቃኝበት ዓመት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ስለ ኤርትራ

ፕሬዝዳንቱ የኤርትራ ሕዝብ ነጻነቱን ለመቀዳጀት ለ50 ዓመታት ያደረገውን ትግል አሞግሰዋል።

ኤርትራን በሃይማኖት ለመከፋፈል፣ በምጣኔ ሀብት ለማዳከም እንዲሁም የተለያዩ አሉታዊ ሙከራዎች ቢደረጉም የኤርትራን ሕዝብ "ፖለቲካዊ ንቃተ ሕሊና ያዳበሩ" እንጂ ያወኩ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

"ለ50 ዓመታት ከተደረገው ትግል የተገኘው ተሞክሮና ትምህርት" ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደተሸጋገረ በንግገራቸው ጠቅሰዋል።

ኤርትራ "ሽብርን ትደግፋለች" በሚል ሽፋን የተጣሉባትን ማዕቀቦች ሳይኮንኑም አላለፉም።

ኤርትራ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ ነጻነት እንደተሸረሸረ እና ሰብአዊ መብትን የሚጥሱ አፈናዎች በመንግሥት እንደሚፈጸሙ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋቾች ቢተቹም፣ የኤርትራ መንግሥት ግን እነዚህን ውንጀላዎች አይቀበላቸውም።