የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባይደን የነጭ የበላይነት "መርዛማ" ነው ሲሉ ወቀሱ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በፋሎ በተሰነችው የኒው ዮርክ ክፍለ ግዛት ተገኝተው የነጭ የበላይነትን አወገዙ።

ፕሬዝደንት ባይደን የነጭ የበላይነት "በሰውነታችን የሚዘዋወር መርዝ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

በበፋሎ ከተማ ባለፈው ቅዳሜ በተፈፀመ ጥቃት አንድ ግለሰብ 10 ጥቁር አሜሪካዊያንን መግደሉ ተዘግቧል።

በዘር ጥላቻ የተፈፀመ ነው የተባለውን ጥቃት ያደረሰው አንድ የ18 ዓመት ነጭ አሜሪካዊ ነው።

ተጠርጣሪው ፋሺስትና የነጭ የበላይነት አምላኪ መሆኑን የሚገልጥ መዝገብ በይነ መረብ ላይ ለጥፏል።

ፕሬዝደንት ባይደን ይህን ጥቃት አስታከው ማክሰኞ ዕለት ወደ በፋሎ አቅንተው ሃዘን ደርሰዋል።

ጥቃት አድራሹ "በጥላቻ ከታወሩ አናሳዎች" መካከል ነው ሲል ወርፈዋል።

በጥቃቱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ያጡ ቤተሰቦችን ቀርበው ያነጋገሩት ባይደን "የነጭ የበላይነት ቦታ የለውም" ብለዋል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ተጠርጣሪው 320 ኪሎ ሜትር ተጉዞ የመጣው ይህን ጥቃት ለማድረስ እንደሆነ ገልጠዋል።

መርማሪዎች እንዳሉት ተጠርጣሪው ባይገታ ኖሮ የተጨማሪ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፍ ነበር።

ታጣቂው ማኒፌስቶ ብሎ በይነ መረብ ላይ በሰቀለው ሃተታ የሤራ ትንታኔዎችን እያጣቀሰ የነጭ የበላይነትን አመክንዮ ለማልበስ ይሞክራል።

ባይደን ግለሰቡ በፍራቻና ዘረኝነት የታጠረ፤ ጥላቻውን ምክንያት አድርጎ ጥቃት ማድረሱን አውግዘዋል።

ባይደን፤ በፈረንጆቹ 2017 ቨርጂኒያ ውስጥ የደረሰው ተመሳሳይ ጥቃት ለፕሬዝደንት መቀመጫው እንዲወዳደሩ እንዳነሳሳቸው አውስተዋል።

በግል ሕይወታቸው ከባድ የሚባል ሃዘን አስተናግደው የሚያውቁት ባይደን በርካቶችን ሲያጽናኑ ታይተዋል።

ባይደን የመጀመሪያ ባለቤታቸውና የ13 ዓመት ልጃቸውን በመኪና አደጋ እንዲሁም ከወንድ ልጆቻቸው መካከል አንዱን በካንሰር አጥተዋል።

በጥቃቱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ያጡ ሰዎች አሁን በሞት የተለይዋቸው ሰዎች አንድ ቀን ፈገግ ማለታቸው እንደማይቀር የሚያስረግጥ ንግግር አድርገዋል።

የአካባቢው ሰዎች ፕሬዝደንቱ ላደረጉት የማጽናናት ሥራ አመስግነው መንግሥት ጉዳዩን አንድ እንዲለው አሳስበዋል።

ነገር ግን ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የጦር መሣሪያ ቁጥጥርን በተመለከተ ማድረግ የሚችሉት ውሱን ነው።

የጦር መሣሪያ ቁጥጥርን በተመለከተ ኮንግረሱን ለማሳመን የበኩሌን አደርጋለሁ ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ቢሆንም ይህን ማድረግ ለፕሬዝደንቱ ቀላል የሚባል አይደለም።

ሃገር በቀል ሽብርተኝነትን በተለመከተ ጠበቅ ያለ ሕግ ቢኖርም "እውነታውን መጋፈጥ ግን ይኖርብናል" ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደንና የኒው ዮርክ ዴሞክራት እንደራሴዎች ፕሬዝደንቱን ታከው ከተማዋን ጎብኝተዋል።