የናይጄሪያ አየር መንገዶች በአውሮፕላን ነዳጅ ጭማሪ ምክንያት የሀገር ውስጥ በረራዎችን ሊያቆሙ ነው

መንገደኞች በአውሮፕላን ላይ ሲሳፈሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የናይጄሪያ አየር መንገዶች የአውሮፕላን ነዳጅ ጭማሮን በመቃወም ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የሃገር ውስጥ በረራዎችን ሊያቆሙ ነው።

በተያዘው አመት ብቻ አራት እጥፍ ገደማ መጨመሩን ያስታወቀው የናይጄሪያ አየር መንገድ ኦፕሬተሮች (ኤኦኤን) ይህንም ሁኔታ መቋቋም አልተቻለም ብሏል።

"በአለም ላይ ያለ የትኛውም አየር መንገድ ቢሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ አይነት አስደንጋጭ አጨማመርን ሊቋቋም አይችልም። ከዚህ ማገገም አይቻልም" ብሏል።

ለጭማሬው ዋነኛ ምክንያት የሆነው ሩሲያ በየካቲት ወር ዩክሬንን መውረሯ ነው።

የናይጄሪያን ዘጠኝ የሃገር ውስጥ አየር መንገዶችን የሚወክለው የናይጄሪያ አየር መንገድ ኦፕሬተሮች (ኤኦኤን) አየር መንገዶቹ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ አገልግሎታቸውን እየሰጡ የነበሩት በድጎማ ነበር ብሏል።

ከመጋቢት ወር ጀምሮ በርካታ የበረራዎች መሰረዝ እንዲሁም መዘግየቶች የነበሩ ሲሆን ይህም አብዛኛውን ጊዜ ከአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።

የአውሮፕላን ቲኬቶች ዋጋም በአንዳንድ አየር መንገዶች በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በሶስት እጥፍ ጨምሯል።

በናይጄሪያ ያሉ መንገደኞች በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመጣው የሃገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ናይራ ነው ቲኬት የሚገዙት። ነገር ግን ነዳጅ አቅራቢዎች የሚከፈሉት በአሜሪካን ዶላር ነው።

ናይጄሪያ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ የነዳጅ አምራች ብትሆንም ከሞላ ጎደል ሁሉንም የአውሮፕላን ነዳጇን ከውጭ ታስገባለች።

አኦኤን ለመንግስት፣ ለፓርላማ አባላት፣ ለመንግሥታዊው የነዳጅ ኩባንያ እና ነዳጅ ሻጮችን ለሚወክለው ማኅበር የነዳጁን ዋጋ ዝቅ ለማድረግ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አስረድቻለሁ ብሏል።

የዋጋ ጭማሮው በመንገደኞች ላይ ጫና መፍጠር የለበትም ሲል የሚከራከረው ተቋሙ "ቀድሞውንም ብዙ ችግሮች እያጋጠሟቸው በመሆኑ" የዋጋው ጫና እነሱ ጫንቃ ላይ ማረፍ የለበትም ብሏል።

ስለታቀደው የስራ ማቆም አድማ መንግሥት እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።