"የእንግሊዝ መንግሥት ወደ አምባገነኗ ሩዋንዳ ይልከኝ ይሆን? “ ኤርትራዊው ታዳጊ

ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፕሮግራም ወደ ካሌ ከተማ ሳቀና ስደተኞች በሚበዙባት በዚህች የወደብ ከተማ ቁማር ቤት አያለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር።
የፈረንሳይዋ የወደብ ከተማ ካሌ በቁማር ባትታወቅም ነገር ግን ከሆቴሌ ውጭ የሚገኘው ቁማር ቤት ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው እንግሊዝ መድረስን እንደ ሎተሪ የሚቆጥሯትን ስደተኞችን ልናገኝ እንደሆነ አስታወሰኝ።
ስደተኞቹ ቤቶች በሚሏቸው ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ የተወሰነ ጊዜ አሳለፍን።
በአውሮፓውያኑ 2016 እነዚህ የስደተኛ መጠለያ ድንኳኖች፣ የክርታስ እና የላስቲክ ደሳሳ ጎጆዎች በይፋ በባለስልጣናቱ እንዲፈርሱ ቢደረጉም የረድዔት ድርጅቶች አሁንም ቢሆን 1 ሺህ 500 የሚሆኑ ስደተኞች እንደሚኖሩ ነገሩን።
የተሻለ የወደፊትን ፍለጋ

በነዚህ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ያሉ በሙሉ በማለት በሚቻል ሁኔታ ወደ እንግሊዝ የመግባት ህልም አላቸው። ስሙ እንዲቀየር የጠየቀንና ኢርፋን ብለን የምንጠራው ኤርትራዊ ታዳጊ ሁኔታው ተመሳሳይ ቢሆን ታሪኩ ለየት ያለ ነው።
ሌሎቹ አንድ ላይ ቢሆኑም ታዳጊው ብቻውን ነበር። በአስተርጓሚም ታሪኩን እንደተረዳነው የትውልድ ሃገሩን ኤርትራን፣ መንደሩንና ቀዬውን ለቆ የወጣው ከ18 ወራት በፊት ነው። ጉዞው ፈተናና ውጣ ውረድ የተሞላበት ነበር። በዚህ አደገኛው ጉዞው የሊቢያን በረሃ አቆርራጧል፣ ጣልያንና ቤልጂየምንም ተሻግሯል ።
የ16 አመቱ ታዳጊ የተሻለ ህይወትን ፍለጋ ሃገሩን ለቆ እንደወጣ ተናግሯል።
"ኤርትራ ውስጥ ነፃነት የለም። ማንኛውም ሰው 18 አመት ሲሞላው ወደ ግዳጅ የወታደራዊ አገልግሎት መግባት አለበት " ሲል ይናገራል።
ወደ እንግሊዝ ለመግባት እየጠበቀ ያለው ይህ ታዳጊ ከሰሞኑ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሩዋንዳ መካከል ተደረሰ የተባለው ስምምነት ምን አይነት ተፅእኖ ይፈጥርበት ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአንድ ቲኬት ወደ ሩዋንዳ
ከሰሞኑ በካሌ በኩል ተጭነው ወደ እንግሊዝ የሚያቋርጡ አዲስ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳያቸው በሩዋንዳ እንዲታይ ህይወታቸውንም በዚያ ይጀምራሉ ተብሏል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አዲሱ ፖሊሲ ግለሰቦች እነዚህን አስቸጋሪ ጉዞዎች እንዳያደርጉ ያግዳቸዋል ብሏል።
ነገር ግን ተሟጋቾች እንደሚሉት እንደ ኢርፋን ያሉ ሰዎች ወደ ብሪታንያ ለመድረስ በጀልባ እና በጭነት መኪናዎች አቆራርጠው ለመሄድ የተነሱ ናቸው ምክንያቱም በእንግሊዝ መሬት ላይ እስካልሆኑ ድረስ ጥገኝነት መጠየቅ ስለማይችሉ ነው።
ኢፍራን ከሁለት ወራት በላይ ከቤተሰቡ ጋር እንዳልተነጋገረ ነገረን። "ቤተሰቦቼ የት እንዳለሁ አያውቁም። ምንም አይነት ግንኙነት የለም."ይላል
በካሌ ውስጥ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከሚረዱ በርካታ የእርዳታ ኤጀንሲዎች በአንዱ የሚሰራው አስተርጓሚያችን የኢፍራንን ታሪክ ሲተረጉምልን ማልቀስ ጀመረ።
አንገቱን ደፍቶ እየተንሰቀሰቀ ነበር። ደህንነቱን ስጠይቀው፤ አዎንታውን በሚገልጽ መልኩ አንገቱን ነቀነቀ። አስተርጓሚው ሃሳቡን ሰብስቦም ንግግራችንን ቀጠልን።
"ወንድሞቼ እና እህቶቼ ናፍቀውኛል። ከአንድ አመት ተኩል በላይ በመንገድ ላይ ነኝ,። ምን እንደደረሰባቸው አላውቅም" በማለት አስተርጓሚው ቀደም ሲል ያስለቀሰውን የኢፍራንን ታሪክ ነገረን።.

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ተገኝተህ ወደ ሩዋንዳ ብትላክ ምን ታደርጋለህ? "ስል ጠየቅኩት
ኢርፋን " እንግሊዝ የህግ ሃገር ናት" ሲል መለሰ
" የእንግሊዝ መንግሥት ወደ ሩዋንዳ ይልከኝ ይሆን?" እዚያ እኮ አምባገነን ነው"
" እዛ መቆየት አለብህ ካሉ በሩዋንዳ የምቆይ አይመስለኝም"
ሩዋንዳ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ባሉ በርካታ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ነፃነት የሌላትና ጨቋኝ አገር ተደርጋ ትቆጠራለች።
ከአውሮፓውያኑ 1994 ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በሩዋንዳ የጎሳ ግጭት እና የዘር ማጥፋትን ተከትሎ አገሪቱን በማረጋጋት ቢሞገሱም አገሪቱን በአንድ ፓርቲ ብቻ በበላይነት እየመሩ ነው በሚል ክስ ሲቀርብባቸው ይሰማል።
ኑሮ በካሌ ድንኳን ውስጥ

ኢርፋን በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ለመጠየቅ ቆርጧል ምክንያቱ በፈረንሳይ ካለው የተሻለ እንክብካቤ እንደሚደረግለት ስላመነ።
ካሌ የአውሮፓ የስደት ቀውስ ተምሳሌት ከሆነች አመታት ተቆጥረዋል ። በርካቶች ከካሌ አደገኛ በሆነ ሁኔታ በጀልባዎች ፣ በጭነት መኪኖች ወይም በባቡር ጭነቶች ተደብቀው ወደ እንግሊዝ ለመድረስ ይሞክራሉ።
በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2016 የፈረንሳይ ባለስልጣናት ጊዜያዊ መጠለያዎችን ከማፍረሳቸው በፊት ኸልፕ ሬፊጅስ በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባደረገው ቆጠራ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች እዚያ ይኖሩ እንደነበር ግምቱን አስቀምጧል።
በአሁኑ ወቅት ኢርፋን እና ሌሎች ስደተኞች በድንኳኖች፣ በተተው ህንፃዎች፣ በድልድዮች ስርና በጊዜያዊ መጠለያዎች ይኖራሉ።
ሁኔታዎች አሰቃቂ ናቸው ለነዚህ ነዋሪዎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን የማግኘት ሁኔታቸውም የተገደበ ነው።
ማንም ሰው ቢሆን በእንዲህ አይነት መልኩ መኖር አይፈልግም ግን እየኖሩ ነው እግሊዝም አዲስ ተስፋን ታመጣልናለች ብለው እየጠበቁ ነው።
"በብሪታንያ ሰዎች እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፣ ትምህርት ቤት መሄድ ይችላሉ" ይላል።
የዩክሬን ስደተኞች
በእርዳታ ኤጀንሲዎች እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እገዛ በካሌ ውስጥ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ከነዚህ መጠለያዎች ውጭ ያለውን ህይወት ያውቃሉ። በተለይም የዩናይትድ ኪንግድም ባለስልጣናት የዩክሬን ስደተኞች አያያዛቸው ላይ ጥያቁዎች ተነስተዋል።
"ከዩክሬናውያን ጋር መወዳደር አንችል። እነሱ ያረፉት በሆቴል ውስጥ ነው" ሲል ያነጋገረን አንድ ወጣት ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"እነሱ (የአውሮፓ ባለስልጣናት) ስለ ዩክሬን ሰዎች በሚያስቡበትና በሚጨነቁበት መንገድ ለእኛ ደንታ የላቸውም." ይላል።
"ሩዋንዳ ሊልኩልን ቢሞክሩ ማንም አይቀበለውም" ሲልም ያክላል
ያገኘናቸው ወጣቶች የወደፊቱ ብሩህ እንደሚሆን ያምናሉ። በአደገኛ ሁኔታ አቆራርጠው የመጡበትም ሁኔታ ቀን ወጥቶላቸው ይረሱት ይሆናል።
"ህይወት ከባድ ናት ነገርግን መቻልን እንማራለን። ሁሉም ነገር ደህና ይሆናል" ይላል ኢርፋን።
እሱም ሆነ ሌሎቹ መቼ እና እንዴት ደህና ይሆናል የሚለውን አያውቁም።












