ነጥብ የተቀነሰበት የዋይኒ ሩኒ ቡድን ወደ ሶስተኛው ሊግ ወረደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንጋፋው እንግሊዛዊ እግር ኳስ ተጫዋች ዋይኒ ሩኒ የሚያሠልጥነው ደርቢ ካውንቲ ወደ ሶስተኛው ሊግ ወረደ።
ራምስ በተሰኘው ቅጥል ስማቸው የሚታወቁት ደርቢዎች በኪውፒአር ተረተው ወደ ሶስተኛው ሊግ ወርደዋል።
ደርቢ ካውንቲ በፈረንጆቹ 1986 ወደ ላይኛው ሊግ ከወጣ በኋላ ወደ ሶስተኛው ሊግ ሲወርድ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ደርቢ ካውንቲ ለዚህ ቀውስ የተዳረገው የቀድሞው ባለቤቱ ሜል ሞሪስ ክለቡን ማስተዳደር አልችልም ብለው ለመንግሥት አሳልፈው ከሰጡት በኋላ ነው።
ወደ ሶስተኛው ሊግ የወረደው ዋይኒ ሩኒ "መቼም ባለቤቱ ይህን እያዩ እንቅልፍ ባይነሳቸው ነው የሚገርመኝ" ሲል መረር ያለ አስተያየት ሰጥቷል።
ደርቢ ካውንቲ ባለፈው መስከረም 12 ነጥብ ተቀንሶበት ከነበረበት 12ኛ ደረጃ ወደ ወራጅ ቀጣና መውረዱ ይታወሳል።
ነገር ግን የዋይኒ ሩኒ ልጆች ከረዥምና አድካሚ ትግል በኋላ እጅ ሰጥተዋል።
"ክለቡን አመሰቃቅሎት ነው የሄደው። ሜል ሞሪስ የደርቢ ደጋፊ እንደሆነ አውቃለሁ። በብስጭት እየጨሰ እንደሆነ አልጠራጠርም" ሲል ሩኒ ቃሉን ለቢቢሲ ሰጥቷል።
"ይህ እንዳይሆን የቻልነውን ሁሉ አድርገናል። ከሚገባው በላይ ለፍተናል። ብስጭታችን የሚበርድ አይደለም።"
ደርቢ ካውንቲ መስከረም ላይ ከተጣለበት የ12 ነጥብ ቅጣት በተጨማሪ ባለፈው ኅዳር ተጨማሪ 9 ነጥብ ተቀንድቦበታል።
የዋይኒ ሩኒ ቡድን 21 ነጥብ ባይቀነስበት ኖሮ 24 ቡድኖች ባሉት ሁለተኛው የእንግሊዝ ሊግ 17ኛ ደረጃ ላይ ይቀመጥ ነበር።
"በዚህኛው ሊግ የሚያቆየን ነጥብ ነበረን። በዚያ ላይ በጣም ጥሩ ብቃት ያላቸው እዚሁ ያደጉ ተጫዋቾች አፍርተን ነበር" ሲል ውጤቱ ያንገበገበው ሩኒ ተናግሯል።
"በጣም ተበሳጭቻለሁ። እጅግ አዝኛለሁ። ነገር ግን በክለቡ በጣም እኮራለሁ። ተስፋ ያለው ቡድን ሠርተናል።"
የእንግሊዝና ማንችስተር ዩናይት ቁጥር አንድ ጎል አስቆጣሪው ሩኒ ጫማ የሰቀለው ባለፈው የውድድር ዘመን ነበር።
ሩኒ ወደ ደርቢ ካውንቲ የመጣው በአሠልጣኝነትና ተጫዋችነት ቢሆንም ሙሉ በሙሉ የአሠልጣኝነት ወንበሩን ተቆጣጥሮ ክለቡን ሲመራ ቆይቷል።
ባለፈው የውድድር ዘመን እንዲሁ ከመውረድ ያዳነውን ክለብ ታሪክ ዘንድሮ ግን ሊደግመው አልቻለም።
ነገር ግን ቀውስ ያለ ቡድንን መንፈሰ ጠንካራና ታጋይ እንዲሆን በማድረጉ ብዙዎች ያወድሱታል።
ያደገበት ክለብ ኤቨርተን ባለፈው ጥር አሠልጣኝ አድርጎ ይቀጥረዋል ተብሎ ቢታማም ሩኒ ግን ከደርቢ ጋር መቆየትን መርጧል።
የአንጋፋው ተጫዋች ስም አሁን ደግሞ አሠልጣን ሾን ዳይሽን ካሰናበተው በርንሊ ጋር እየተያያዘ እየተነሳ ነው።
ነገር ግን አዲሱ የደርቢ ካውንቲ ባለቤት ክሪስ ክሪችነር ሩኒ ከክለባቸው ጋር እንደሚቆይ ተናግረዋል።
ከደርቢ ጋር የአንድ ዓመት ውል የሚቀረው ሩኒም በሚቀጥለው ዓመት ለሚገጥመው ፈተና እንደተዘጋጀ ጠቆም አድርጓል።
አሜሪካዊው አዲሱ የደርቢ ባለቤት ክሪስ ክሪችነር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ክለቡን ለመግዛት የተስማሙት።
የደርቢ ካውንቲ ሜዳ የሆነው ፕራይድ ፓርክ አሁንም ባለቤትነቱ በሜል ሞሪስ እጅ ነው።












