ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሳልፈልግ ልደቴ ተከብሮልኛል ያለው አሜሪካዊ መስሪያ ቤቱን ከሶ 450 ሺህ ዶላር አሸነፈ
በአሜሪካ ኬንታኪ ግዛት በሚገኝ አንድ መስሪያ ቤት የሚሰራው ግለሰብ ልደቴ ሲከበር ለጭንቀት ይዳርገኛል ስለዚህ ያንን ለማድረግ እንዳትሞክሩ ሲል አስጠነቀቀ። መስሪያ ቤቱን ግን ይህንን ማስጠንቀቂያ ችላ አለው።
እንዳውም የተዋጣለት ድግስ አዘጋጅተው 'ሰርፕራይዝ' አደረጉት።
እሱ ግን ከመደሰት ይልቅ ፕሮግራሙን ጥሎ ሄደ። ከዚህ በኋላ ከመስሪያ ቤቱ ጋር አለመግባባት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ፍርድ ቤት ሄዶ ከሰሰ። ፍርድ ቤቱም መስሪያ ቤቱን ጥፋተኛ ብሎ 450 ሺህ ዶላር እንዲከፈለው ወሰኗል።
ከሳሹ ኬቨን በርሊንግ ይባላል። በሚሰራበት ግራቪቲ ዲያግኖስቲክስ ማዕከል በ2019 የተከበረለት ልደት ለከፍተኛ የመንፈስ መታወክ ወይም 'ፓኒክ አታክ' እንደዳረገው ተናግሯል።
የከሰሹ በርሊንግ የጥብቅና ኩባንያ በጤና እክል ምክንያት አድሎአዊ ድርጊት ተፈጽሟል የሚል ክስ አቅርቧል። ሆኖም ተከሳሹ ኩባንያ ምንም የፈጸምኩት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት የለም ብሏል።
በቀረበው ክስ መሠረት የአእምሮ መታወክ የሚያስቸግረው በርሊንግ መስሪያ ቤቱ በመደበኝነት ለሌሎች ሰራተኞቹ ከሚያደርገው በተቃራኒ የኔን ልደት እንዲያከብር አልፈልግም ሲል ለሥራ አስኪያጁ መናገሩን ይገልጻል።
የዚህም ምክንያቱ ልደቱ ሲከበር በልጅነቱ የነበሩት መጥፎ ትዝታዎችን ተቀስቅሰው ለአእምሮ መታወክ ስለሚዳርገው ነው።
ይህንን የበርሊንግ ጥያቄ ግን ጉዳዬ ያለው አልነበረም። የኮቪድ-19 ምርመራ የሚሰጠው ኩባንያው እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ልደቱን ደግሰው ጠበቁት። ድርጊቱ በርሊንግን ወዲያው ለአእምሮ መታወክ ዳረገው። ወዲያምውም ፕሮግራሙን ጥሎ ሄደ።
በርሊንግን እና መስሪያቤቱን ለመካሰስ የዳረጋቸው ቀጥሎ ባለው ቀን የተፈጸመው ድርጊት ነው። ክሱ እንደሚያመላክተው በርሊንግ በማግስቱ በተደረገው ስብሰባ ላይ ወቀሳ ቀረበበት።
"የስራ ባልደረቦችህን ደስታ ቀምተሃል። የትንሽ ልጅ ድርጊት ነው የፈጸምከው" የሚል ወቀሳ ሰነዘሩበት። ይህ ድርጊት ሰውዬውን ለዳግም የአእምሮ መታወክ ዳረገው። በዚህም ለቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ወደ መስሪያ ቤት እንዳይመጣ ነገሩት።
ሰውዬው በሶስተኛው ቀን ወደ መስሪያቤቱ ሲመለስ የስራ ቦታ ደህንነት እናስቀድማለን በሚል ከስራ ተሳናበተ። በዚህም ሳቢያ የጤና እክልን መሰረት ያደረገ መድሎ ተፈጸሞብኛል እና ፍትሃዊ ያልሆነ ውሳኔ የሚል ክስ መሰረተ።
ባለፈው ወር መገባደጃ በነበረው የሁለት ቀን የፍርድ ሂደት ዳኞች 300 ሺህ ዶላር ለደረሰበት የስሜት መናወጥ 150 ሺህ ደግሞ ካሳ በድምሩ 450 ሺህ እንዲከፈለው በይነዋል።
የኩባንያው ዋና ኦፕሬሽን ቢሮ ሃላፊ ጁሊ ብራዚል ለሀገር መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ በርሊንግን የተባረረው የስራ ቦታ የስነ ምግባር ደምብን ጥሶ ነው ብለዋል።
"በክስተቱ የተጎዱት ሰራተኞቼ እንጂ ከሳሹ አይደሉም" ያሉት ሀላፊዋ ኩባንያው ውሳኔውን ለማስቀየር እየሰራ እንደሆነ እና ይግባኝ መጠየቁን አስረድተዋል።
የበርሊንግ ጠበቃ ቶኒ ቡቸር "በግራቪቲ ውስጥ ለሚሰራ ማንኛውም ሰው ስጋት የሆነ እና ከስራ መባረርን የሚያስከትል ስጋት ስለመኖሩ ምንም አይነት ማስረጃ አልቀረበም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የመንፈስ መታወክ ነበረበት። ያለው ነገር ያ ብቻ ነው። የየግራቪቲ ዲያግኖስቲክስ ሰራተኞች ያለበትን ችግር ስላልተረዱ እና በድርጊቱ ስላልተደናገጡ ያንን ስጋት አድርገው ገምተውታል" የሚሉት ጠበቃ ቡቸር "የአእምሮ ጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ምንም አይነት ማስረጃ ሳይኖር አደገኛ ናቸው ብሎ ማሰብ አድሎአዊ ነው" ሲሉ አብራርተዋል፥
መረጃዎች እንደሚያ መላክቱት ከ 40 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን የአእምሮጤና እክል እንዳለባቸው የሚያሳይ ሲሆን 20 በመቶ የሚሆነው የእምሮ መታወክ ያጋጥመዋል።