ኢላን መስክ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የአክሲዮን ድርሻ ከትዊተር ገዛ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢላን መስክ ከትዊተር የአክሲዮን ድርሻ 9.2 በመቶ መግዛቱን የዎል ስትሪት ሰዎች አረጋገጡ።
ይህን ተከትሎ ሰኞ ዕለት በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ የትዊተር አክሲዮን ሽያጭ 27 በመቶ አሻቅቦ ውሏል።
የቴስላ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢላን ከፈረንጆቹ መጋቢት 14 ጀምሮ ከግዙፉ የማሕበራዊ ድር አምባ ድርሻዎች የ73.4 ሚሊዮን ባለቤት ይሆናል ማለት ነው።
ሰኞ ዕለት በነበረው የአክሲዮን ገበያ መሠረት ኢላን መስክ የገዛው የአክሲዮን ድርሻ በዶላር ሲተመን 2.89 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል።
አሁን ኢላን መስክ የትዊተር ትልቁ ባልድርሻ ሆኗል።
የትዊተር ፈጣሪ ጃክ ዶርሲ ከገዛ ፈጠራው ያለው የአክሲዮን ድርሻ መጠን 2.25 በመቶ ነው።
80 ሚሊዮን ተከታዮች ያካበተው ኢላን ትዊተርን አብዝተው ከሚጠቀሙ ሰዎች መካከል ነው።
ነገር ግን በቅርቡ የራሱን ማሕበራዊ ድር አምባ ሊገነባ እንደሆነ የሚጠቁም ወሬ አውርቶ ነበር።
ባለፈው ወር መስክ ተከታዮቹን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ሲል ለጥፎ ነበር።
"ትዊተር ነፃ ንግግርን ያበረታታል ብላችሁ ታስባላችሁ?" የሚል ጥያቄ አስከትሎ ከተከታዮቹ አስተያየት ሲሰበስብ ተስተውሏል።
"ነፃ ንግግር የዲሞክራሲ የጀርባ አጥንት ነው። ትዊተርን ይህን መርህ ይከተላል ብላችሁ ታስባላችሁ?"
ኢላን በዚህ አልተገታም። ቀጥሎ ሌላ ጥያቄ አስከተለ።
"አዲስ ማሕበራዊ ድር አምባ ያስፈልገናል ብላችሁስ ታስባላችሁ?"
ኢላን ብዙዉን ጊዜ ስፔስኤክስ ስለተሰኘው ኩባንያው ዜና በትዊተር ገፁ ያሠራጫል።
አንዳንዴ ጊዜ ደግሞ አወዛጋቢ የሚባሉ ሐሳቦችን በመጫርም ዝናን አትርፏል።
ባለፈው ዓመት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ 2 በመቶ የኢላን ሃብት የዓለም ሕዝብን ይመግባል ማለታቸውን ተከትሎ የተፈጠረው የሚረሳ አይደለም።
ይህን የሰማው ኢላን ሰውዬው እንዴት አድርጎ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ረሃብን እንደሚገታ ካሳዩኝ ገንዘቡን እሰጣለሁ ሲል መልሶ ነበር።
የኢላን መስክ መኪና አምራች ኩባንያ ቴስላ ተመኑ አንድ ትሪሊዮን ደርሷል።
ይህም ከማይክሮሶፍት፣ አማዞን፣ የጉግሉ አልፋቤትና አፕል ቀጥሎ አምስተኛው ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጣ ድርጅት አድርጎታል።
ኢላን ባለፈው ኅዳር የኤሌክትሪክ መኪና ከሚያመርተው ድርጅቴ የአክሲዮን ድርሻ ልሽጥ ወይ ሲል የትዊተር ሰዎችን ጠይቆ ነበር።
ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለዚህ ጥያቄ ምላሻቸውን ሰጥተው 58 በመቶው አዎ በማለታቸው 5 ቢሊዮን የሚያወጣ ድርሻ መሸጡ የሚዘነጋ አይደለም።












