ባይደን ለችግር ጊዜ ከተከማቸው ነዳጅ በርካታ ሚሊዮን በርሜል እንዲቀዳ አዘዙ

ታትሟል

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አሜሪካ ለችግር ጊዜ በሚል ካከመቻችው ነዳጅ በገፍ እንዲቀዳ አዘዋል።

ፕሬዝደንቱ ይህን ትዕዛዝ ያስተላለፉት እየናረ የመጣውን የነዳጅ ዋጋ ለመዋጋት ነው።

ባይደን እንዲወጣ ያዘዙት 180 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ በማከማቻው ታሪክ ትልቁ ነው።

ዩክሬን ባለው ጦርነት ምክንያት ጣራ እየነካ የነበረው የነዳጅ ዋጋ ከባይደን ትዕዛዝ በኋላ ትንሽ ረገብ ብሏል።

ነገር ግን አሜሪካ በየቀኑ ለመከራ ጊዜ ካስቀመጠችው ነዳጅ አንድ ሚሊዮን በርሜል ብትቀዳም ችግሩን ሙሉ በሙሉ አይቀርፈውም ይላሉ የዘርፉ ሰዎች።

ባይደን፤ ከማከማቻው እንዲቀዳ የታዘዘው ነዳጅ አሜሪካ "የራሷን የነዳጅ ምርት እስክታሳልጥ ድረስ" እንዲያግዝ በሚል ነው ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ ኩባንዎች ነዳጅን ከመንግሥት መውሰድ የመጨረሻ አማራጭ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ባይደን አረንጓዴ የኃይል ምንጭ የሚከተሉ ኩባንያዎች እንዲበረታቱ መክረዋል።

በሚቀጥለው ኅዳር የግማሽ ዓመት ምርጫ ለማካሄድ ደፋ ቀና እያለች ያለችው አሜሪካን ጨምሮ የዓለም ሃገራት የኑሮ መወደድ እያማረራቸው ነው።

ባይደን፤ ስትራቴጂክ ፔትሮሊዬም ሪዘርቭ ከተሰኘው የችግር ቀን ገንዳ ነዳጅ ለመቅዳት የወሰንነው "ያለዕቅዳችን" ነው ብለዋል።

ይህ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻ ገንዳ የተመሠረተው በፈረንጆቹ 1974 ነው።

ማከማቻው ቴክሳስና ሉዊዚያና መካከል በሚገኘው የገልፍ ኮስት ላይ በተንጣለለው የጨው ክምር አካባቢ ይገኛል።

ይህ ገንዳ በፈረንጆቹ 2009 700 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ አቅፎ ነበር። ባለፈው መጋቢት ሲለካ ግን የነዳጅ ክምችቱ ወደ 568 ሚሊዮን በርሜል ወርዷል።

አሜሪካ ከሳዐዲ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ግዙፍ የነዳጅ አምራች ከሆነችው ሩሲያ ነዳጅ አልገዛም ካለች ወዲህ የነዳጅ እጥረት እያንገላታት ይመስላል።

የነዳጅ ዋጋ መለከያ የሆነው ብሬንት ክሩድ ባለፈው የፈረንጆቹ ወር መጀመሪያ ዋጋ አሜሪካና አጋሮቿ ሩሲያ ላይ ማዕቀብ ከጣሉ በኋላ አሿቅቧል።

ምንም እንኳ የኃይል ዋጋ ቀስ በቀስ ቢወርድም ነዳጅ ግን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዋጋው 70 በመቶ ጨምሯል።

አሜሪካ ውስጥ እየናረ የመጣው ኑሮ ሪፐብሊካን ጮቤ እንዲረግጡ እያደረጋቸው ነው። የባይደን ተቃዋሚዎች የኑሮ ውድነቱን በባይደን አስተዳደር አላከዋል።

አሁን ደግሞ ነዳጅ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዋጋው ሲያሻቅብ የባይደን አስተዳደርን ከድጡ ወደ ማጡ መርቷቸዋል።

ባለፈው ሐሙስ ሩሲያን ጨምሮ የነዳጅ አምራች ሃገራት ማሕበሩ ኦፔክ አባላት የነዳጅ ምርታቸውን ለመጨመር ተስማምተዋል።

የኃይል ዋጋ ከዩክሬን ጦርነት በፊትም ቢሆን የዓለም ምጣኔ ሃብትን ሊፈታተነው እንደሚችል ግምት ነበር።