132 ሰዎችን አሳፍሮ የተከሰከሰው የቻይና ቦይንግ 737 አውሮፕላን ያጋጠመው ምንድን ነው?

ታትሟል

132 ሰዎችን ያሳፈረ የቻይና የመንገደኞች አውሮፕላን በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በሚገኝ ደናማ የተራራ አካባቢ ወድቆ ተከሰከሰ።

የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ኩሚንግ ከተባለው ከተማ ወደ ጓንግዡ እየተጓዘ ሳለ ጓንግዢ ግዛት ውስጥ ወድቆ በመከስከስ በእሳት ተያይዟል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች አሃዝና የአደጋውን ምክንያት በተመለከተ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ነገር ግን የነፍስ አድን ሠራተኞች ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ስለመኖራቸው ያገኙት ምንም አይነት ምልክት የለም።

በአሁኑ ጊዜ የቻይና አየር መንገዶች በአጠቃላይ ጥሩ የሚባል የደኅንነት ታሪክ ያላቸው ሲሆን፣ የመጨረሻው ዋነኛ አደጋ ያጋጠመው ከ12 ዓመታት በፊት ነበር።

ሰኞ የደረሰው አደጋ በመላዋ ቻይና ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የአደጋውን ምክንያት ለማወቅ አስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግ አዘዋል።

የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ አደጋውን ተከትሎ ያሉትን ሁሉንም ቦይን 737-800 አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ ማድረጉ ተዘግቧል።

የበረራ መረጃ እንዳመለከተው አውሮፕላኑ መሬት ላይ ወድቆ ከመከስከሱ በፊት ከበረራ ከፍታው በፍጥነት አሽቆልቁሎ ነበር።

ከአደጋው በኋላ ከ600 በላይ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በአደጋው ስፍራ ተሰማርተዋል። የእሳት አደጋ ሠራተኞች ከሁሉ ቀድመው በቦታው የደረሱ ሲሆን ከአደጋው ጋር ተያይዞ በኮረብታማ አካባቢው የተከሰተውን እሳት ለመቆጣጠር ችለዋል።

በነዋሪዎች የተቀረጹና በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም በቻይና መገናኛ ብዙኃን የተሰራጩ ቪዲዮዎች በአደጋው ስፍራ እሳትና ጭስ እንዲሁም የአውሮፕላኑ ስብርባሪዎችን አሳይተዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ ተከታታይ አደጋዎች ካጋጠሙ በኋላ በቻይና ውስጥ በአየር ትራንስፖርት ደኅንነት እና የደረጃ ላይ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። በዚህም ባለፉት አስር ዓመታት ከፍ ያለ ለውጥ በመታየቱ አደጋዎች የተለመዱ አይደሉም።

ባለፉት ዓመታት ዋነኛ የተባለው የአየር ትራንስፖርት አደጋ ያጋጠመው ከ10 ዓመት በፊት በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንያት በተከሰከሰ አውሮፕላን 42 ሰዎች የሞቱበት ክስተት ነው።

አሁን አደጋው ያጋጠመው የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ በአደጋው ሐዘኑን የገለጸ ሲሆን በአውሮፕላኑ ውስጥ ስለተሳፈሩ ሰዎች መረጃ ለመስጠት የስልክ መስመር አዘጋጅቷል።

የቻይና መንግሥት ንብረት የሆነው አየር መንገዱ በከቻይና ሳውዘርን እና ከኤር ቻይና ጋር በአገሪቱ ካሉ ሦስት ግዙፍ አየር መንገዶች መካከል የሚጠቀስ ነው።

የቻይና ሲቪል አቪዬስን አስተዳደር አደጋውን ተከትሎ መርማሪዎችን ወደ አደጋው ስፍራ መላኩን ገልጿል።

ይህ ቦይንግ 737 አውሮፕላን በበረራ ቁጥር ኤምዩ5735 በቻይና የሰዓት አቆጣጠር ከእኩለ ቀን በኋላ ከኩንሚንግ ተነስቶ ወደ ጓንግዡ እያመራ ነበር።

የበረራ ተከታታይ ድረ ገጾች እንዳሉት አውሮፕላኑ በአየር ላይ ከአንድ ሰዓት በላይ ቆይቶ የነበረ ሲሆን፣ ወደ መድረሻው ዉዡ ሲቃረብ ዝቅ ብሎ ነበር። መዳረሻው በዚህ ወቅት ከባድ ጎርፍን የሚያስከትል የአየር ሁኔታ የሚከሰትበት እንደሆነም ተነግሯል።

ነገር ግን በአካባቢው የነበረው የአየር ሁኔታ ምንም እንኳን ዳመናማ ቢሆንም አደጋው በተከሰተበት ጊዜ ለዕይታ አስቸጋሪ ሁኔታ አልነበረም ተብሏል።

የበረራ መከታተያ መረጃ አውሮፕላኑ በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሜትሮችን ማሽቆልቆሉን አመልክተዋል።

'ፍላይትራዳር24' የተባለው የበረራ መረጃ እንዳለው አውሮፕላኑ በ29,100 ጫማ ከፍታ ላይ ሲበር ቆይቶ፣ ከሁለት ደቂቃ ከ15 ሰከንዶች በኋላ ወደ 9,075 ጫማ ወርዷል። ስለአውሮፕላኑ በመጨረሻ የተገኘው መረጃ በ3,225 ጫማ ላይ ሳለ ነው።

በረራ መረጃ የሚያቀርበው ድረ ገጽ እንደሚለው አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን ቦይንግ 737-800 በአገልግሎት ላይ ለሰባት ዓመት የቆየ ነው።

ይህንን አውሮፕላን ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢንዶኔዢያና በኢትዮጵያ አውሮፕላኖች ላይ አሰቃቂ አደጋን ካስከተለው እጅግ ዘመናዊው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ሞዴል ቀደም ብሎ የተሰራ ነው።

ቻይና ከአደጋዎቹ በኋላ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ከበረራ ማገዷ ይታወሳል።

ቦይንግ አሁን ቻይና ውስጥ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ "በመገናኛ ብዙኃን በኩል ስለአደጋው የወጣውን ዘገባ አይተናል፣ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ እየሰራን ነው" ብሏል።