‘ፑቲን ቢገደሉ ጦርነቱ ያበቃል’ ያሉት የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ቁጣን ቀሰቀሱ

ፀረ ፑቲን ተቃውሞ በተለያዩ ቦታዎች ቢሰሙም የሩሲያ ባለሥልጣናት የምክር ቤት አባሉ ባሉት ላይ ቁጣቸውን ገልጸዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፀረ ፑቲን ተቃውሞ በተለያዩ ቦታዎች ቢሰሙም የሩሲያ ባለሥልጣናት የምክር ቤት አባሉ ባሉት ላይ ቁጣቸውን ገልጸዋል
ታትሟል

አንድ የአሜሪካ የምክር ቤት አባል (ሴናተር) የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ሰዎች ፑቲንን ስለመግደል እንዲያስቡ መናገራቸው ተሰምቷል።

ሊነድሴ ግራሃም የተባሉት ሴናተር ሲናገሩ "ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ለማስቆም ብቸኛው አማራጭ የሆነ ሰው ፑቲንን ሲያስወግድ ብቻ ነው'' ብለዋል።

በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፖለቲከኛው ሩሲያውያን ቭላድሚር ፑቲንን የሚከዳ ሰው ይኖራት ይሆን? ብለዋል። በዚህም ጦርነቱ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ትልቅ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የሴናተሩ ንግግር ታዲያ በአሜሪካ የሩሲያውን አምባሳደር በእጅጉ አስቆጥቷቸዋል።

ደቡባዊ ካሊፎርኒያን የሚወክሉት ሴናተር ሊንድሴ ግራሃም በትዊተራቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ ፑቲንን የሚደግል ሰው አገሩንም ሆነ ዓለምን በእጅጉ ነው የሚጠቅመው ብለዋል።

"ሩሲያ ውስጥ ብሩተስ ይኖር ይሆን? በእጅጉ የተሳካለት ኮሎኔል ስታፈንበርግ የሩሲያ መከላከያ ውስጥ የለም እንዴ?" ሲሉም ጠይቀዋል።

ብሩተስ በሮማውያን ታሪክ ውስጥ ታላቁን ንጉስ ጁሊየስ ቄሳርን ከድቶ የገደለው የቅርቡ ሰው ሲሆን፣ ኮሎኔል ስታፈንበርግ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1944 ላይ የጀርመኑን መሪ አዶልፍ ሂትለር ለመግደል የሞከረ ወታደራዊ መኮንን ነው።

በአሜሪካ የሩሲያው አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ የሴናተሩን አስተያየት "ተቀባይነት የሌለውና አሳፋሪ ነው'' በማለት ገልጸውታል። አክለውም አሜሪካ ውስጥ ያለው ፀረ ሩሲያ አስተሳሰብና ጥላቻ በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል።

"የአንዲት አገር ሴናተርና ስለ ሞራል ልዕልና የሚያወራ አንድ ፖለቲከኛ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት የዋሺንግተንን ግብ ለማሳካት በሚል ሽብርተኝነትን ሲያውጁ ማየት ለማመን ከባድ ነው።"

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ የዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ በሩሲያ ፖለቲከኞችና በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ጭምር ማዕቀብ መጣላቸው የሚታወስ ነው።

ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ የኔቶ አባል አገራትን እንደምትከላከል የገለጹ ሲሆን ወደ ዩክሬን ወታደሮችን መላክ የሚለውን ግን እንደ አማራጭ እንደማያዩት ገልጸዋል።

ትናንት አርብ ዕለት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ሳኪ በሰጡት መግለጫ የሴናተሩ አስተያየት የግላቸው እንጂ የአሜሪካንን መንግሥት የማይወክል እንደሆነ ገልጸዋል። አክለውም እንዲህ አይነት አስተያየት በምንም አይነት ሁኔታ ከእዚህ አስተዳደር የሚመጣ አይደለም ብለዋል።

የሴናተር ሊነድሴ ግራሃም አስተያየት በአሜሪካ የሩሲያን አምባሳደር ብቻ ሳይሆን የሩሲያ ቃል አቀባዩ ዲሜትሪ ፔስኮቭንም አስቆጥቷል።

"እውነት ነው፤ በአሁኑ ወቅት በርካቶች ትክክለኛ አስተሳሰብ ላይ ያለ ጭንቅላት እየተጠቀሙ አይደለም'' በማለት ሩሲያውያን ሕብረታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል ቃል አቀባዩ።