ሩሲያ እና ዩክሬን፡ በፖለቲካ ምክንያት ስፖርተኞችን ማገድ ተገቢ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዓለም አቀፉ የፓራሊምፒክ ኮሚቴ (አይፒሲ) በዩክሬን ላይ ከፈጸመችው ወረራ ጋር በተያያዘ ሩሲያ ላይ እገዳ የጣለ ሌላኛው የስፖርት ውድድር ሆኗል።
የ2022 የቤጂንግ የክረምት ፓራሊምፒክ ሊከፈት 24 ሰዓት ሲቀረው የሩሲያ እና የቤላሩስ ስፖርተኞች እንዳይሳተፉ ማገዱን አስታውቋል።
ሩሲያ ባለፉት ቀናት ብቻ ከ2022ቱ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከመታገድ እስከ 'ፎርሙላ ዋን' የሩሲያ ታላቁ ውድድርን እስከ ማጣት ድረስ በርካታ ቅጣቶችን አስተናግዳለች።
በዓለም ዙሪያ ያሉ የስፖርት ሰዎች እና ድርጅቶች ቅጣቶቹን እንደሚደግፉ ቢገልጹም የቅጣቶቹ ፍትሃዊነት ላይ ግን ጥያቄ ተነስቷል።
"አድሏዊ ድርጊት"
አይፒሲ ስፖርተኞቹን መቅጣቱን በመቃወም የሩሲያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ መግለጫ አውጥቷል።
"በዚህ ውሳኔ መሠረት የሩሲያ ስፖርተኞች አሁን ባለው ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ወንጀለኞች ሆነው ተቆጥረዋል" ብሏል ኮሚቴው።
የአይፒሲ ፕሬዝደንት አንድሪው ፓርሰንስ በበኩላቸው "ተፅዕኖ ከተፈጠረባቸው አገራት ለመጡ የፓራ ሊምፒክ ስፖርተኞች መንግሥታችሁ ባለፈው ሳምንት የኦሊምፒክ መርህ በመጣስ በወሰዳቸው ውሳኔዎች በመጎዳታችሁ በጣም እናዝናለን። . . . የተጎዳችሁት በመንግሥታችሁ ምክንያት ነው" ብለዋል።
የሩሲያ እግር ኳስ ማኅበር ደግሞ የሩሲያ ቡድኖችን ከውድድር ማግለል "አድሏዊ ነው" ሲል ገልጾ የፊፋን ውሳኔ በሕጋዊ መንገድ እንደሚሞግት አስታውቋል።
ድርጅቱ በመግለጫው "[ውሳኔው] አድሏዊ እና እጅግ በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸውን ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞች፣ የክለቦች እና የብሔራዊ ቡድን ሠራተኞች እንዲሁም ከሁሉም በላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሩሲያውያን ደጋፊዎችን ይጎዳል" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ከስፖርት መንፈስ ጋር ይቃረናል"
ከስፖርተኞች መካከል የቀድሞ የፎርሙላ ዋን ተወዳዳሪ ዳኒል ክቪያት በትዊተር ገጹ ላይ የሩሲያን ስፖርተኞች ማገድ ከስፖርት መንፈስ ጋር ይቃረናል ብሏል።
ክቪያት ጦርነቱን በተቸበት ጽሑፉ "በወንድማማች አገራት መካከል ግጭት በማየቴ በጣም አሳዝኖኛል" ሲል አስፍሯል።
"ነገር ግን ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሁሉንም የስፖርት ፌዴሬሽኖች ስፖርት ከፖለቲካ ውጪ እንዲሆን እና የሩሲያ አትሌቶች እና ቡድኖች በዓለም ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ መከልከላቸው ኢ-ፍትሃዊ ከመሆኑ ባለፈ ስፖርት የሚያስተምረንን የአንድነት እና የሠላም መርኅ የሚቃረን መሆኑን ለማጉላት እና ለማሳወቅ እፈልጋለሁ" ሲል አክሏል።
የሞተር ስፖርት አስተዳዳሪ አካል የሆነው ኤፍአይኤ የሩሲያ ስፖርተኞች በውድድሮች ላይ እንዲካፈሉ ቢፈቅድም በአገር ውስጥ እንዳይወዳደሩ እገዳዎች ተጥለዋል።
በፎርሙላ ዋን ብቸኛው የሩሲያ ተወካይ የሆነው ኒኪታ ማዜፒን የዩናይትድ ኪንግደም የሞተር ስፖርት በስተላለፈ ውሳኔ መሰረት በሐምሌ ወር ከሚደረገው 'የብሪቲሽ ግራንድ ፕሪ' ውጪ ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"የዩክሬን ወረራ ትልቅ ኢፍትሃዊነት ነው"
በሲድኒ በሚገኘው የማኩዋሪ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ታሪክ ምሁር የሆኑት ዶ/ር ኪት ራትቦን ለቢቢሲ እንደገለጹት ስፖርታዊ እገዳው ላይ የተነሳው የፍትሃዊነት ጥያቄ ትክክል ነው።
"ስፖርተኞቹ አገራቸው በምታደርገው ጉዳይ ላይ አይወስኑም። ስለዚህ መወሰን በማይችሉት ነገር ቅጣት ይጠብቃቸዋል ማለት ነው።"
ስፖርተኞች እንደ ጦርነት ባሉ ቀውሶች ወቅት ከተለያዩ ችግሮች ሊጠበቁ እንደማይችሉ ራትቦን ጨምረው ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
"ለምሳሌ በሩሲያ ባንኮች እና ኢንዱስትሪዎች ላይ ማዕቀብ ሲጣል ብዙ ሰዎች ያለ ምርጫቸው ይጎዳሉ" ሲሉም አክለዋል።
"የዩክሬን ወረራ በስፖርተኞች ላይ ከሚደርሰው ግፍ የበለጠ ትልቅ ኢፍትሃዊነት ነው። ስፖርትና ፖለቲካ አይገናኙም እያልን በማስመሰል መቀጠል አንችልም" ብለዋል።
ከስኬታማ ፓራሊምፒያኖች መካከል አንዷ የሆነችው ብሪታኒያዊቷ ታኒ ግሬይ-ቶምፕሰን በበኩሏ ለሩሲያ ስፖርተኞች እንደምታዝን ገልጻ ሆኖም ውሳኔውን ትክክለኛ እርምጃ ነው ብላለች።
"በሩሲያ ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ህይወት ከባድ ነው። አብዛኛዎቹ ስፖርተኞችም ራሳቸውን የሚደገፉት ባሸነፉት ሜዳሊያ ብቻ ነው" ስትል ግሬይ-ቶምፕሰን ለቢቢሲ ስፖርት ተናግራለች።
"በጣም ከባድ ቢሆንም ግን ስፖርት እና ፖለቲካ ያልተገናኙ በማስመሰል መቀጠል አንችልም።"
"አይፒሲ ለመወዳደር ፈቃደኛ ያልሆኑ በርካታ አገራት ይገጥሙት ነበር። ሁሉም የሜዳሊያ ሥነ ሥርዓቶች ይረበሹ ነበር" ስትልም አክላለች።
የዓለም ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች የሆነው ዳኒል ሜድቬዴቭን ጨምሮ አንዳንድ የሩሲያ ስፖርተኞች በጥቃቱ ምክንያት ሞስኮን በይፋ የተቹበት አጋጣሚዎች ነበሩ።
ራትቦን ግን ስፖርተኞችን የማገድ ውሳኔዎች በግለሰብ ምላሾች ላይ መመርኮዝ የለባቸውም ይላሉ።
"ጉዳይን በመተንተን ትክክለኛውን መልዕክት የሚያስተላልፍ አይመስለኝም" ሲል ራትቦን ያስረዳሉ።
"ጠንካራው መልዕክት "ከዩክሬን እስክትወጣ ድረስ ሩሲያ ታግዳለች" የሚለው ነው" ብለዋል።
የስፖርት እገዳዎች ውጤታማ ናቸው?
ያለፉትን ምሳሌዎች ካየን ስፖርታዊ እገዳዎች ጦርነትን ማስቆምም ሆነ ኢፍትሃዊነትን ከስር መሰረቱ እንደማይፈቱ ያሳያሉ።
በመንግሥት የሚደገፈው የዘር መድልዎ እአአ በ1991 በይፋ ከማብቃቱ በፊት ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ዘመን ለአስርት ዓመታት ከስፖርት ውድድር ታግዳ ቆይታለች።
በተመሳሳይም ዩጎዝላቪያ ከ1992 የአውሮፓ ዋንጫ መገለሏ በባልካን አገራት የደረሰውን ዘግናኝ ጥቃት አላቆመውም።
ራትቦን ግን ስፖርታዊው ማዕቀብ ትልቅ ምሳሌያዊ መልዕክት እንዳለው ያምናሉ። ለዚህ ደግሞ ስፖርት በሩሲያ የቅርብ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወቱን ያነሳሉ። አገሪቱ የ2014 የክረምት ኦሊምፒክ እና የ2018ቱን የዓለም ዋንጫን ማስተናገዷ ይታወሳል።
"ስፖርት ለሩሲያ እና ለፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጠንካራ መሣሪያ ሆኖ ቆይቷል" ሲሉም ይከራከራሉ።
"ምንም ያህል ቢዘገይም የስፖርት ተቋማት ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እየገመገሙ ከሆናቸው አዎንታዊ እርምጃ ነው።"
















