4 ሺህ ቅንጡ መኪናዎችን የጫነች መርከብ ሰጠመች

ታትሟል

4 ሺህ ቅንጡ መኪናዎችን የጫነች መርከብ በፖርቹጋል ባህር ውስጥ ሰጠመች

በሺዎች የሚቆጠሩ ቅንጡ መኪናዎችን ይዛ አዞሬስ ደሴቶች ላይ የሰጠመችው ዕቃ ጫኝ መርከብ በዚሁ ጉዞ ላይ ሳለች ከሁለት ሳምንታት በፊት እሳት ተቀስቅሶባት ነበር።

ፌሊሲቲ አሴ የተሰኘችው ይህቺ መርከብ ወደ 4,000 የሚጠጉ እንደ ፖርሽ እና ቤንትሊ ያሉ የቅንጦት መኪኖችን ይዛ ከጀርመን ኤምደን ወደብ ወደ አሜሪካ ሮድ አይላንድ በመጓዝ ላይ ሳለች ነበር በእሳት የተያያዘችው።

እሳቱ ከሁለት ሳምንት በፊት በመርከቧ ላይ በተነሳ ወቅት ሁሉም የመርከቡ ሰራተኞች ከመርከቡ እንዲሸሹ ተደርጓል።

ፋያል ደሴት አቅራቢያ የወደብ አስተዳደር ሃላፊ የሆኑት ጆአዎ ሜንዴስ ካቤካስ እስካሁን ከመርከቧ የነዳጅ ፍሰት ስለማጋጠሙ ሪፖርት እንዳልተደረገ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ሆኖም መርከቧ 3,500 ሜትር ጥልቀት ባለው የአትላንቲክ ውቅያኖስ የታችኛው ክፍል ላይ በምትደርስበት ጊዜ የነዳጅ ታንከሮቹ ሊጎዱ ይችላሉ የሚል ስጋት መኖሩን ገልጸዋል።

የፖርቹጋል የባህር ሃይል መርከቧ ላይ በተነሳው እሳት ሳቢያ የተጎዳ ሰው አለመኖሩን ገልፆ 22ቱ የመርከብ ሰራተኞች ወደ ሆቴል መወሰዳቸውን ጠቁሟል።

ሰራተኞቹን ከመርከቡ ለማስወጣት በአካባቢው ሲጓዙ የነበሩ አራት የንግድ መርከቦች እና የፖርቹጋል አየር ሃይል በጋራ መስራታቸውንም አመላክቷል።

የቅንጡ መኪናዎቹ አምራች የሆነው ቮልስዋገን በተሽከርካሪዎቹ ላይ የደረሰው አደጋ በኢንሹራንስ የተሸፈነ መሆኑን ገልጿል። ለመኪኖቹ ኢንሹራንስ ወደ 155 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ሊሆን እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል።

ቤንትሊ 189 መኪኖቹ በመርከቧ ላይ እንደነበሩ ያረጋገጠ ሲሆን ፖርሽ በበኩሉ 1,100 የሚሆኑ መኪኖቼ መርከቧ ላይ ተጭነው ነበር ብሏል።