ሕጻን ልጇ በገዛ ፍቅረኛዋ የተገደለባት እናት 16 ወራት እስር ተፈረደባት

እናት ረበካና ሟች ልጇ ራይደር

የፎቶው ባለመብት, SUBMITTED

የምስሉ መግለጫ, እናት ረበካና ሟች ልጇ ራይደር
ታትሟል

ወንድ ልጇ በገዛ ፍቅረኛዋ የተገደለባት አሜሪካዊት እናት 16 ወራት እስር ተበይኖባታል፡፡

ይህ የኾነው በአሜሪካ አወዛጋቢ ከሚባሉ ክሶች አንዱ በሆነው ‹ልጅን ያለመከላከል ቸልተኝነት ወንጀል› ጥፋተኛ ኾና በመገኘቷ ነው፡፡

እናት ረበካ 29 ዓመቷ ነው፡፡ ሟች ልጇ ራይደር ይባላል፡፡ ገና የ2 ዓመት ሕጻን ነበር፡፡

የሚኖሩት በኦክላሆማ ግዛት ሲኾን ፍቅረኛዋ ልጇን ራይደርን መግደሉ ከተረጋገጠ በኋላ እናት ብትሆንም ልጇን ከሞት ማዳን ወይም መከላከል ባለመቻሏ ፍርድ ቤት በ16 ወራት እስራት ትቀጣ ሲል ብይን አስተላልፏል፡፡

ለሦስት ወራት ያህል እስር ቤት ስለነበረች ከዚህ በኋላ 13 ወራት እዚያው እንደምትከርም ይጠበቃል፡፡

ፍርድ በተሰጠበት ዕለት ረበካ በሰጠችው ቃል ልጇን ከሞት ለመከላከል የምትችልበት አንዳችም ዕድል እንዳልነበረ አስረድታለች፡፡

‹‹እጅግ የምኮራበት ቆንጅዬ፣ ብልህ፣ ጠንካራና ጤነኛ ልጅ ነው የነበረኝ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሕይወቴን በሐሴት ሞልቶት ነበር፡፡ አሁን ልጄን አጥቼ በጤና ያለሁት የልጄ ገዳይ ፍቅረኛዬ በሕይወት እንደሌለ በማወቄ ብቻ ነው›› ብላለች፡፡

ፍርዱን የበየኑባት ዳኛ ማይክል ቱፐር በበኩላቸው ‹‹እስር ቤት መበስበስ ያለብሽ እናት አይደለሽም፣ ጭራቅ አይደለሽም፣ ለራስሽ ክብር ያለሽ፣ ዋጋ ያለሽ ሴት ነሽ›› ሲሉ አሞካሽተዋታል፡፡

ከዚያም በኋላ ነው የ16 ወራት ቀላል እስር የበየኑባት፡፡

የረበካ፣ የፍቅረኛዋና የሟች ሕጻን ልጇ ጉዳይ ላለፉት ወራት በአሜሪካ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡት ቆይቷል፡፡

በተለይ በሴቶች መብት ተቆርቋሪዎች ዘንድ እናት በልጇ ሞት ጥፋት ሳይኖርባት መታሰሯ የግፍ ግፍ ነው በሚል ለረበካ ድምጽ ሲያሰሙላት ነበር፡፡

ኾኖም በኦክላሆማ ግዛት ልጆቻቸውን ከጥቃት መከላከል ያልቻሉ ወላጆች ከአጥፊው እኩል ይቀጣሉ የሚል ሕግ በመኖሩ ረበካ ልጇን አጥታ ለቅሶዋን ግን እስር ቤት እንዲሆን ሆናለች፡፡

የሁለት ዓመት ልጇ ራይደር ቤት ውስጥ ሞቶ የተገኘው እናት ረበካ በምትሠራበት መሥሪያ ቤት በሥራ ላይ ሳለች ነው፡፡

ፍቅረኛዋ ክሪስቶፈር ትሬንት ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ በመሰወሩ ሁኔታው ለፖሊስ ጥርጣሬን ያጭርበታል፡፡

ከሕጻን ራይደር ሞት 4 ቀናት በኋላ ፖሊስ የእናት ረበካን ፍቅረኛ በዊቺታ ተራራ ላይ ያገኘዋል፡፡

ኾኖም የሟች ሕጻን እናት ረበካ፣ ፍቅረኛዋ ክርስቶፎር፣ በዚያ የተራራ ጫካ ውስጥ የተገኘው በሕይወት ሳይሆን ሞቶ ነው፡፡

ራሱን ከገደለበት ዛፍ ሥር አንድ ማስታወሻ የተወ ሲኾን፣ ‹‹ፍቅረኛዬ ረበካ በልጇ ሞት ተጠያቂ አይደለችም፤ እሷ ንፁህ ሴት ናት›› የሚል ነበር፡፡

ፖሊስ ቆይቶ በምርመራ እንዳረጋገጠው የሕጻን ራይደር የሞት ምክንያት ጾታዊ ጥቃት እንደሆነ ደርሶበታል፡፡

ሕጻኑን ደግሞ የረበካ ፍቅረኛ ክሪስቶፈር እንደገደለው በተጨማሪ ምርመራዎች በማያሻማ ሁኔታ ተረጋግጧል፡፡

እናት በልጇ ሰውነት ላይ ከዚያ በፊት መጠነኛ መጫጫሮችን የተመለከተች ቢኾንም ፍቅረኛዋ ክርስቶፎር የሕጻናት የጾታ ጥቃት አመለኛ እንደሆነ ግን ፍጹም ጠርጥራ አታውቅም ነበር፡፡