ቻይና የኔፓልን ድንበር አልፋ ገብታለች-ሪፖርት

የፎቶው ባለመብት, Namkha Rural Municipality
የኔፓል መንግሥት ሪፖርት ቻይና የኔፓልን ድንበር አልፋ ገብታለች ሲል ከሷል።
ለቢቢሲ ሾልኮ በደረሰው በዚህ ሪፖርት መሰረት ቻይና የሁለቱን ሃገራት ድንበር አልፋ የገባችው በሁለት አቅጣጫዎች ነው።
ቻይና በግዛቴ ውስጥ ጣልቃ ገብታለች የሚል ክስ ከኔፓል ሲቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ለህዝብ ይፋ ባልተደረገ ሪፖርት ነው።
ባለፈው መስከረም ወር ላይ ቻይና ከኔፓል በስተምዕራብ በምትገኘው ሁምላ ግዛትን አልፋ ገብታለች የሚለውን ክስ ተከትሎ የወጣ ሪፖርት ነው።
በካትማንዱ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ድንበሩን አልፎ የመግባት ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም ብሏል።
የኔፓል መንግሥትም ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ሪፖርቱ እስካሁን ለህዝብ ይፋ ያልሆነበት ወይም ያልታተመበት ምክንያት ግልጽ አይደለም።
ነገር ግን የኔፓል መንግሥት ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት በቅርብ አመታት አሻሽሏል።
የሪፖርቱ ግኝቶች ከቤጂንግ ጋር እየጎለበተ ያለው ግንኙነት ላይ ጫና ያሳድራሉ ተብሏል።
ኔፓልና ቻይና በሂማሊያ ተራሮች በኩል ድንበራቸው የሚዋሰን ሲሆን ወደ 1 ሺህ 400 ኪሎሜትር ርቀትን ይሸፍናል።
የሁለቱ አገራትም ድንበር የተሰመረው በ1960ዎቹ ሲሆን በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረሙ ተከታታይ ስምምነቶችንም ተከትሎ ነው።
አብዛኛው የድንበር ስፍራ በተራራማ ሰንሰለት ላይ በመሆኑ ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ነው። በመሬት ላይ ያለው ድንበር በኪሎሜትሮች ልዩነት በተሰነጣጠሉ ምሰሶዎች ተከፋፍሏል።
ይህም ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ ድንበሩ የት ጋር እንደሆነ በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ቻይና ድንበሩን አልፋ ገብታለች የሚለውንም ተከትሎ የኔፓል መንግሥት አንድ ግብረ ኃይል ወደ ሁምላ ልኳል። አንዳንዶች ቻይና የኔፓልን ድንበር አልፋ ህንፃዎች እንደገነባች ይናገራሉ። ግብረ ኃይሉ የፖሊስ እና የመንግሥት ተወካዮችን ያካተተ ነበር።
ለቢቢሲ በድብቅ በተሰጠው ሪፖርት መሰረት የቻይና የጸጥታ ኃይሎች የክትትል እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነና በኔፓል ድንበር ላይ ላንግጆንግ በሚባል ቦታም ሃይማኖታዎ እንቅስቃሴዎች መገደቡን አስፍሯል።
አካባቢው በሂንዱዎችና ቡድሂስቶች የተቀደሰ ነው ከሚባለው በቻይና ከሚገኘው የካሊሽ ተራራ አቅራቢያም ስለሚገኝም በርካቶችም ሃይማኖታዊ ጉዞዎችን ያደርጋሉ።
ሪፖርቱ አክሎም ቻይና የኔፓል አርሶ አደሮች ግጦሽ እንዳያካሂዱ ገድባለች።
ነገር ግን ግብረ ኃይሉ በመጀመሪያ በኔፓል ውስጥ ተሠርተዋል ተብሎ የሚታሰበው የቻይና ሕንፃዎች በኔፓል እንዳልተገነቡና በቻይና ውስጥ መገንባታቸውን አረጋግጧል።
መርማሪዎቹ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ኔፓላውያን ስለ ድንበር ጉዳዮች ለመነጋገር ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ደርሰውበታል ምክንያቱም አንዳንዶቹ ከድንበሩ ባሻገር ባለው የቻይና ገበያዎች ጋር የገበያ ትስስርም ስላላቸው ነው።
ሪፖርቱ የደህንነት ዋስትና ለመስጠት የኔፓል የጸጥታ ሃይሎች በአካባቢው እንዲሰፍሩ መክሯል።
በተጨማሪም ኔፓልና ቻይና እነዚህን መሰል የድንበር ጉዳዮችን ለመፍታት አዲስ አሰራርም እንዲዘረጉ ጠቁሟል።












