የአይኤሱ መሪ የአሜሪካንን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እራሱንና ቤተሰቡን ማጥፋቱ ተነገረ

አቡ ኢብራሂም አል-ሃሺሚ አል-ቁራይሺ

የፎቶው ባለመብት, US DEPARTMENT OF STATE

የምስሉ መግለጫ, አቡ ኢብራሂም አል-ሃሺሚ አል-ቁራይሺ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ጦር ልዩ ኃይል አባላት በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) መሪን ዒላማ በማድረግ እርምጃ መውሰዳቸውን ተከትሎ የአይኤሱ መሪ እራሱንና ቤተሰቡን ማጥፋቱ ተገለጸ።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ወታደራዊ ተልዕኮውን ተከትሎ ባወጡት መግለጫ "ለጦር ኃይል አባሎቻችን ጀግንነት እና ክህሎት ምስጋና ይድረስ፤ አቡ ኢብራሂም አል-ሃሺሚ አል-ቁራይሺን ከጦር ሜዳ አስወግደናል" ብለዋል።

አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን፣ የአይኤስ መሪው ድንገተኛ የአሜሪካ ጥቃትን ተከትሎ እራሱን እና የቤተሰቡን አባላት በቦምብ አጥፍቷል ብለዋል።

የሶሪያ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ይህን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ 13 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው የአሜሪካ ጦር አውሮፕላኖች በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ በምትገኘው ኢድሊብ ግዛት አትሜህ ከተማ ረቡዕ ጥር 24/2014 በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ሌሊት ላይ አርፈዋል።

በስፍራው የነበሩ ሰዎች የአሜሪካ ጦር አባላት ከፍተኛ የሆነ መከላከል ገጥሟቸው ነበር ሲሉ ተናግረዋል። የጦር አባላቱ መኪና ላይ ከተገጠሙ ፀረ-አውሮፕላን መሳሪያዎች ከፍተኛ ተኩስ ተከፍቶባቸው ነበር።

ከፍተኛው የተኩስ ድምጽም የአሜሪካ ሄሊፕፍተሮች አካባቢውን ለቀው እስኪሄዱ ድረስ ለሁለት ሰዓታት ቀጥለው ነበር።

ኒው ዮርክ ታይምስ ከአሜሪካ ሄሊኮፕተሮች መካከል አንዱ የመካኒካል ችግር ካጋጠመው በኋላ የጦር አባላቱ ጥለውት ሄደው አሜሪካ ዳግም በወሰደችው የአየር ጥቃት ሄሊኮፕተሩ እንዲጋይ ተደርጓል ሲል ዘግቧል።

ፕሬዝደንት ባይደን በዚህ የአይኤስ መሪን ዒላማ ባደረገው ተልዕኮ ላይ የተሳተፉ አሜሪካውያን በሙሉ በሰላም ተልዕኳቸውን አጠናቀው ተመልሰዋል ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ የተልዕኮው ዓላማ የአሜሪካውያን እና የአጋሮቿን ሕዝብ ደኅንነት ለመጠበቅ እና ዓለምን የተሻለ ደኅንነት ያለባት ለማድረግ ነው ብለዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

1px transparent line

የሶሪያ ሲቪል ዲፌንስ የአሜሪካ ጦር ዒላማ ባደረገው ሕንጻ የስድስት ሕጻናት እና የአራት ሴቶች አስክሬንን ጨምሮ የ13 ሰዎች አስክሬን ማንሳቱን አስታውቋል።

በጥቃቱ የቤተሰብ አባላቶቿ የተገደሉባት ታዳጊ ሕጻንን በሕይወት መገኘቷንና ለሕክምና ወደ ሆስፒታል እንደተላከች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አስታውቀዋል።

የአሜሪካ ጦር ዒላማ ባደረገው መኖሪያ ቤት ውስጥ ማን ይኖር እንደነበረ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ጦር ዒላማ ባደረገው መኖሪያ ቤት ውስጥ ማን ይኖር እንደነበረ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ከፍተኛው የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን ለሮይተርስ "በተልዕኮው መጀመሪያ ላይ ዒላማ ተደርጎ የነበረው አሸባሪ፣ እራሱን፣ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ የቤተሰቡን አባላት ገድሏል" ብለዋል።

"የዚህን ተልዕኮ ውጤታማነት እየገመገምን ቢሆንም፤ እአአ 2019 ላይ አል ባግዳዲ የተገደለበት ተልዕኮ ላይ እንደተመለከትነው አሁንም የአሸባሪ የፈሪ ስልት እየተተገበረ መሆኑን አይተናል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከአቡ ኢብራሂም አል-ሃሺሚ አል-ቁራይሺ በፊት አይኤስን ሲመራ የነበረው አቡ ባካር አል-ባግዳዲ እአአ 2019 ላይ የአሜሪካ ጦር ድንገተኛ ጥቃትን ተከትሎ ባፈነዳው ቦምብ እራሱን እና ሦስት ልጆቹን መግደሉ ይታወሳል።

ሰሜን-ምዕራብ ሶሪያ የጽንፈኛ ጂሃዲስቶች ጠንካራ ይዞታ ነው።

የአሜሪካ ጦር ዒላማ ያደረገው ባለ ሁለት ወለል መኖሪያ ሕንጻ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ጦር ዒላማ ያደረገው ባለ ሁለት ወለል መኖሪያ ሕንጻ።