ሱዳናውያን ተቃዋሚዎች ከግብፅ ጋር የሚያገናኘውን አውራ ጎዳና ከዘጉ ከሳምንት በላይ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሰሜናዊ ሱዳን ያሉ ተቃዋሚዎች ሱዳንን ከግብፅ ጋር የሚያገናኘውን አውራ ጎዳናን ከዘጉ ከሳምንት በላይ እንደሆናቸው ተዘገበ።
ሱዳናውያኑ ተቃዋሚዎች ሁለቱን አገራት የሚያገናኘውን መንገድ በርካታ ቦታዎች ላይ በመዝጋታቸው ምክንያት ከሱዳን የቁም ከብቶችንና ሌሎች ሸቀጦችን የጫኑ የግብጽ የጭነት መኪኖች ድንበሩን ተሻግረው መሄድ አልቻሉም።
አብዛኞቹ አርሶ አደር የሆኑት ተቃዋሚ ሰልፈኞች በመጀመሪያ ላይ አውራ ጎዳናውን የዘጉት መንግሥት የኤሌክትሪክ ዋጋ ላይ ጭማሪ ካደረገ በኋላ ውሳኔውን ለማስቀየር ነበር።
ነገር ግን ተቃውሞው ቀስ በቀስ እየሰፋ በመሄድ በሱዳን ጦር ሠራዊቱ ያካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ወደ መቃወምና የጦር ኃይሉን በሚደግፉ የአካባቢው የፖለቲካ ኃይሎች እና ግብፅ ላይ አነጣጥሮ ለቀናት ዘልቋል።
ተቃዋሚዎቹ ሱዳንን ከሰሜናዊ ጎረቤቷ ግብፅ ጋር የሚያገናኛትን ዋነኛ መንገድ ከዘጉት አሁን ዘጠነኛ ቀኑ እንደሆነ ተዘግቧል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጩ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት ከካርቱም ተነስቶ አስከ ድንበር ከተማዋ ኢርጊን ድረስ ባለው የበረሃ መንገድ ላይ ማለፍ ያልቻሉ የግብፃውያን ከባድ ተሽከርካሪዎች ቆመዋል።
በተመሳሳይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወደ ግብፅ በሚያመሩት ተሽከርካሪዎች ላይ ተቃውሞዎች እየተሰሙ ሲሆን መኪኖቹ ከሱዳን እንዳይወጡ እየቀሰቀሱ የሚገኙ ሰዎችም በርካታ ናቸው።
በሰሜናዊው የሱዳን ክፍል ያሉ የዴሞክረሲ ለውጥ አቀንቃኞች ወደ ግብፅ የሚላኩት የቁም ከብቶችና ሌሎች የግብርና ምርቶች በሥልጣን ላይ ያለውን ወታደራዊ ኃይልና የሚያንቀሳቅሳቸውን ተቋማት የሚጠቅሙ በመሆናቸው ከአገር መውጣታቸውን አጥብቀው ይቃወማሉ።
ባለፈው ጥቅምት ወር የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ወደ ከፋ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የገባችው ሱዳን፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሥልጣን ላይ ያሉትን የጦር ኃይሉን መሪዎች የሚቃወሙ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎችን እያስተናገደች ነው።
በዋና ከተማ ካርቱምም ወታደራዊ መሪዎቹ ሥልጣን ለሲቪሎች እንዲያስረክቡ የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄድ ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል።
በዚህም ሳቢያ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው የዶክተሮች ቡድን አስታውቋል።












