በአብዬ ግዛት የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ከፍያለው በናይጄሪያዊ ተተኩ

ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ተሰማ እና ሜጀር ጄኔራል ቤንጃሚን ኦሉፌሚ ሳውየርን

የፎቶው ባለመብት, UNISFA

የምስሉ መግለጫ, ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ተሰማ እና ሜጀር ጄኔራል ቤንጃሚን ኦሉፌሚ ሳውየር
ታትሟል

ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ትገባኛለች በሚሏት የአብዬ ግዛት የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጦር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ተሰማ በናይጄሪያዊ ጄኔራል እንደተተኩ የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የናይጄሪያ ጦር አዛዥ የሆኑትን ሜጀር ጄኔራል ቤንጃሚን ኦሉፌሚ ሳውየርን በአብዬ ለድርጅቱ ሰላም አስከባሪ አዛዥ አድርገው መሾማቸውን ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡባት አብዬ ግዛት በተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቲቷ እንዲወጣ ሱዳን መጠየቋን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስማማቱን ባለፈው ዓመት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

በወቅቱ ሱዳን ባወጣችው መግለጫ የኢትዮጵያ ጦር በሌሎች ተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲተካ መስማማታቸውን ብትገልጽም ከየትኛው አገራት እንደሆነ አልተጠቀሰም።

በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ከአብዬ ግዛት እንዲወጡና በሌላ አገር ጦር እንዲተኩ ሱዳን ተመድን በተደጋጋሚ መጠየቋ ይታወሳል።

በወቅቱ የሱዳን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ "የኢትዮጵያ ሠራዊት በምሥራቃዊ የሱዳን ድንበር አካባቢ እየተጠናከረ ባለበት ጊዜ ስትራቴጂክ በሆነው የሱዳን ማዕከላዊ ስፍራ ላይ የኢትዮጵያ ኃይሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ምክንያታዊ አይሆንም" ብሎ ነበር።

በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው የአቢዬ ግዛት የመንግሥታቱ ድርጅት ያሰማራቸው ሰላም አስከባሪዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው።

በዚህ ኃይል ውስጥ በአጠቃላይ 4,190 ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ሰላም አስከባሪዎች የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 3 ሺህ 158 ወታደሮችና ሰባት የፖሊስ መኮንኖች ከኢትዮጵያ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

ተሰናባቹ ሜጀር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ተሰማ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአብዬ ቆይታቸው ወቅት ላሳዩት ትጋት፣ ከፍተኛ አገልግሎትና ውጤታማ አመራር ምስጋናቸውን አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገልጸዋል።

ሜጀር ጄኔራል መሐሪ ዘውዴ ገብረማርያምን ተክተው በ2012 በአዛዥነት የተሾሙት ሜጀር ጄኔራል ከፍያለው በኢትዮጵያ ጦር ውስጥ ከሰላሳ ዓመት በላይ ያስቆጠረ የላቀ የውትድርና ሥራ እንደሰሩም ከተመድ ድረ-ገፅ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሚኒስቴር የምክር ቤት አባል ሆነው አገልግለዋል።

እንዲሁም በአብዬ የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የኢንጂነሪንግ ክፍልን በመምራት እንዲሁም በመከላከያ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ፣ የማዕከላዊ ኮማንደር ምክትል አዛዥ በመሆን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ማገልገላቸው ተገልጿል።

በአውሮፓውያኑ በ2015ም በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ኃይል (አሚሶም) አመራርነትም አገልግለዋል።

ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው ተሰማ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሩሲያ ጦር አካዳሚ 'ኮማንድ ኤንድ ኮንትሮል ኦፍ ሚሊታሪ ዩኒት ኤንድ ፎርሜሽን' ያገኙ ሲሆን የማስተርስ ዲግሪያቸውን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በአሜሪካ ከሚገኘው አሽላንድ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።

ሜጀር ጄኔራል ቤንጃሚን ኦሉፌሚ ሳውየር በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ በሚገኘው የናይጄሪያ ጦር ጦር ትጥቅ ትምህርት ቤት አዛዥ ሆነው አገልግለዋል።

በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ሁለት ጊዜ ብርጌድ አዛዥ በመሆን እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የላይቤሪያ ወታደራዊ ተልዕኮም ላይ የናይጄሪያ ጦር በመምራት መስራታቸው ተገልጿል።

በናይጄሪያ ጦር በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት ጄኔራል ሳውየር በፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እና በመከላከያ እና በስትራቴጂካዊ ጥናቶች ማስተርሳቸውን አግኝተዋል።