የሶማሊያ መንግሥት ቃል አቀባይ የአጥፍቶ ጠፊ ፍንዳታ ጥቃት ደረሰባቸው

መሐመድ ኢብራሂም ሙአሊሙ

የፎቶው ባለመብት, BBC Somali

የምስሉ መግለጫ, መሐመድ ኢብራሂም ሙአሊሙ
ታትሟል

ትናንት የሶማሊያ መንግሥት ቃል አቀባይ በሆኑት መሐመድ ኢብራሂም ሙአሊሙ ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ተሰነዘረባቸው።

ቃል አቀባዩ በጥቃቱ ጉዳት ቢደርስባቸውም በሕይወት መትረፋቸው ተገልጿል።

የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሁሴን ሮብሌ ትናንት እሁድ በተሽከርካሪያቸው ላይ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት የቆሰሉት የመንግስት ቃል አቀባይ "በተረጋጋ የጤና ሁኔታ ላይ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።

በጥቃቱ ወቅት በቦታው የነበሩ የዐይን እማኞች እንደሚሉት አጥፍቶ ጠፊው ፈንጂውን በመሐመድ ኢብራሂም ሙአሊሙ መኪና አቅራቢያ በመሄድ ማፈንዳቱን በመጥቀስ በእርሳቸው ላይ ያነጣጣረ መሆኑን ይናገራሉ።

የቀድሞ የቢቢሲ ጋዜጠኛ የነበሩት ቃል አቀባዩ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ መንገድ ላይ ሳሉ በደረሰው በዚሁ ፍንዳታ ከተጎዱ በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

የአልሸባብ ታጣቂዎች ለጥቃቱ ሃላፊነት ወስደዋል።

ሞአሊሙ በሶማሊያ የቢቢሲ ዘጋቢ ሆነው ለዓመታት የሰሩ ሲሆን የሶማሊያ ጋዜጠኞች ብሄራዊ ማህበር መሪም ነበሩ።

ይህ ጥቃትም ቢያንስ የስምንት ሰዎችን ሕወት ካጠፋው እና በተመሳሳይ በአልሸባብ አማካይነት በሶማሊያ አየር ሃይል ካምፕ እና በዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ከተፈጸመው የመጨረሻው ጥቃት ከቀናት በኋላ የተፈጸመ ነው።

አልሸባብ የሶማሊያን መንግሥት ከአስር ዓመታት በላይ ሲዋጋ የቆየ ሲሆን በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ጠንካራ ኃይል አለው።

ከሰሞኑ የተከሰቱት የቦምብ ጥቃቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በፕሬዚዳንቱ መካከል በዘገየው ምርጫ ምክንያት ለወራት የዘለቀ የፖለቲካ ፍጥጫ ውስጥ ባሉበት ወቅት ነው።

ሶማሊያዊው ጋዜጠኛ ሞሃመድ ሞሃመድ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ሬዲዮ "አሁን የተፈታ ይመስላል" ሲል በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለውን ፍጥጫ ገልጿል።

"የክልል መሪዎች እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ40 ቀናት ውስጥ ምርጫው እንዲደረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል" ሲል ገልጾ ነበር።