የቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ሃውልት በአንድ ግለሰብ በመዶሻ ተመትቶ ጉዳት ደረሰበት

ሃውልቱን በመዶሻ እየመታ ያለ ግለሰብ
ታትሟል

በለንደን የሚገኘው የቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ሃውልት በአንድ ግለሰብ በመዶሻ ተመትቶ ጉዳት ደረሰበት።

'ዘ ቴምፐስት' በተሰኘው የዊልያም ሼክስፒር የተውኔት ፅሁፍ ላይ ያሉትን 'ፕሮስፔሮ'ና 'ኤሪየል' ገጸ ባህርያትን የሚያሳየው ሃውልት የተቀረጸው ኤሪክ ግሪል በሚባል ግለሰብ ሲሆን በቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ውጭም ከአውሮፓውያኑ 1933 ጀምሮ ቆሟል።

ቀራፂው በህይወት እያለ በጻፈው ማስታወሻ ላይ ሴት ልጆቹ ላይ ወሲባዊ ጥቃት ይፈፅም እንደነበር ከማስፈሩ ጋር ተያይዞ ሃውልቱ እንዲወገድ ለብዙ ዓመታት የተቃውሞ ዘመቻ ተደርጓል።

በትናንትናው ዕለት ፖሊስ በስፍራው የተጠራ ሲሆን ከአራት ሰዓት በኋለ ግለሰቡ ከሃውልቱ ላይ እንዲወርድ ተደርጓል።

ግለሰቡ ተቃውሞውን ለመግለፅ ሃውልቱን በሚመታበት ወቅትም "ህፃናት ደፋሪ" እያለ እየጮኸ እንደነበርም በዋናው መስሪያ ቤት የነበሩ የቢቢሲ ሰራተኞች ተናግረዋል።

ሃውልቱን በመዶሻ እየመታ ያለ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የሜትሮፖሊታን ሙዝየም ኦፍ አርት ቃለ አቀባይ ግለሰቡ በእሳት አደጋ ቡድን ታግዞ እንዲወርድ መደረጉን አስረድተዋል።

በወንጀል ክስ ወደ ፖሊስ ጣቢያም ከመወሰዱ በፊትም በአምቡላንስ ሰራተኞች ምርመራ ተደርጓልም ብለዋል።

በሃውልቱ ላይ እንዲሁም በህንፃው ላይ ስለደረሰው ጉዳት እየመረመሩ መሆኑን ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል።

የቢቢሲ ቃለ አቀባይ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

በቅርብ አመታት ውስጥ እንደ ኪው አኖን ያሉ የሴራ ቡድኖች በአውሮፓውያኑ 1940 ህይወቱ ያለፈው ኤሪክ ግሪል የተቀረጹ ሃውልቶች እንዲወርዱ ዘመቻ እያካሄዱ ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት አወዛጋቢ የሚባሉ ሃውልቶች እንዲወርዱ ተቃውሞዎች በብዛት የሚሰሙ ሲሆን በእንግሊዟ ብሪስቶል ግዛት በ17ኛው ክፍለ ዘመን የባርያ አጋዥ የነበረው ኤድዋርድ ኮልስቶንን ሃውልት ለመገርሰስ የሞከሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማሕበረሰቦች ዘንድ በፅንፍ የሚታዩ ታሪካዊ ሃውልቶች በአሁኑ ወቅት ምን አይነት ስፍራስ አላቸው የሚለው ሰፊ ክርክር አስነስቷል።

የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ እጅ መሞቱን ተከትሎ የተቀጣጠለው ተቃውሞ በምዕራባውያን ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው አሳሾች፣ ጦረኛ ነገሥታት ሃውልቶችን እንዲገረሰሱ አነሳስቷል።

ምንም እንኳን እነዚህ ሰዎች ለምዕራባውያኑ ትልቅ ቢሆኑም በአፍሪካውያንም ሆነ በደቡቡ ዓለም ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያና መደፈርን ሌሎች አሳፋሪ ታሪኮችን የፈፀሙ ናቸው።

የቤልጅየሙ ንጉሥ ሊዮፖልድ ኮንጎ ላይ አስር ሚሊዮኖችን ጨፍጭፏል፣ እጅ ቆርጧል፣ ሰቅሏል። አሳሹ ክርስቶፎር ኮሎምበስም እንዲሁ ቀደምት አሜሪካውያንን ጨፍጭፏል፤ ከምድረ ገፅም እንዲጠፉ ብዙ ጥሯል። ሌሎችም ስመ ጥር የሆኑ ምዕራባውያን በርካታ ናቸው።

አውሮፓና አሜሪካ በባርያ ደም እንዲሁም በቅኝ ግዛት በተዘረፈ ንብረት ከመገንባታቸው አንፃር፤ የሚኩራሩበት "ስልጣኔም" ሆነ በጀግንነት የሚያሞካሿቸው ሰዎች ጭቆናን በተጸየፉ የዓለም ሕዝቦች "ዝርፊያና ጭፍጨፋ ስልጣኔ አይደለም" በሚል ተጋልጠዋል።