ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፖሊስ ጥይት የተገደለችው አሜሪካዊ ታዳጊ ህይወቷ ያለፈው በእናቷ እቅፍ ውስጥ ነው
በሎስ አንጀለስ በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት በአጋጣሚ የተገደለችው የ14 ዓመቷ ታዳጊ ህይወቷ ያለፈው በእቅፋቸው ውስጥ እንደሆነ እናቷ ተናገሩ።
ሟቿ ቫለንቲና ኦሬላና-ፔራልታና እናቷ ከገና ሁለት ቀን ቀደም ብሎ በነበረው ዕለት በአንድ ልብስ መሸጫ መደብር ውስጥ በነበሩበት ወቅት ነው ፖሊስ በአንድ ተጠርጣሪ ላይ ተኩስ የከፈተው።
ከፖሊስ የተተኮሰውም ጥይት ግድግዳውን በስቶ ታዳጊዋን መታት። እናቷ ሶሌዳድ ፔራልታ ልጇን እንዲረዷት ፖሊሶችን መማጸኗን ሲገልፉ እያለቀሱ ነበር፤ ሆኖም ፖሊሶቹ አልረዷትም "እዚያው በተኛችበት ጥለዋት4 ሄዱ" ብለዋል።
በጠበቃ በተነበበ መግለጫ ላይ ሶሌዳድ ፔራልታ እሷ እና ልጇ በሰሜን ሆሊውድ በሚገኝ የልብስ መደብር ውስጥ ለተጠሩበት የልደት ድግስ ልብስ ለመግዛት እየሞከሩ በነበረበት ወቅት ከመቀየሪያ ክፍል ውጭ ጩኸት እና ረብሻ እንደሰሙ ተናግረዋል።።
ወዲያውም ተቀምጠው ተቃቅፈው መጸለይ ጀመሩ። ልጇን የሆነ ነገር ሲመታት እንደተሰቸውና ሁለቱም መሬት ላይ መውደቃቸውንም ገልጸዋል።
የቫለንቲና ሰውነት መዝለፍለፉንና ትንሽ ቆይታም እራሷን ሳተች ልጃቸውንም እየነቀነቁ ሊቀሰቅሷት ቢሞክሩም አልተሳካም።
ልጃቸውም በእቅፋቸው ውስጥ እያለች እንደሞተችም እናቷ በሃዘን ተሰብረው ተናግረዋል።
ለእርዳታ ቢጮሁም ማንም አልደረሰላቸውም።
"በመጨረሻም ፖሊሶች ከመጡ በኋላ ወደ መልበሻ ክፍል ወሰዱኝ እና ልጄን እዚያው እንደተጋደመች ጥለዋት ሄዱ። እንዲረዷት ፈልጌ ነበር ነገር ግን ብቻዋን እንደተኛት ትተዋት ሄዱ" ብለዋል።
ሶሌዳድ ፔራልታ ልጅህን እያየህ ህይወቷ ሲያልፍ ማየቱ በተለይም በእቅፍ ውስጥ መሞት ማንኛውም ሰው ሊገምተው ከሚችል በላይ ጥልቅ ህመሞች አንዱ ነው ይላሉ።
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ አዛዥ ሚሼል ሙር ክስተቱትን የተመሰቃቀለ ሲሉ የጠሩት ሲሆን "የተሟላ፣ ግልፅ የሆነ ምርመራ" ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ፖሊስ በመገበያያ መደብሩ ውስጥ አንድ ግለሰብ ከፍተኛ ረብሻ እየፈጠረ ነው እንዲሁም በአንዳንድ ደንበኞችም ላይ ጥቃት አድርሷል የሚል ጥሪም ደርሶት ነበር የመጣው። ረብሻ ሲፈጥር የነበረው ግለሰብ በጥይት ተመትቶ ተገድሏል።
ግለሰቡን አስመልክቶ በተደረገው የአደጋ ጊዜ ጥሪ ተጠርጣሪው ሽጉጥ እንደነበረው የተነገረ ቢሆንም ምንም አይነት መሳሪያ አልተገኘበትም።
ከፖሊስ የተገኘው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ግለሰቡ አንዲት ሴትዮን እያስቸገረ በነበረበት ወቅት ፖሊሶች ሽጉጥ ይዘው ሲከቡት ያሳያል።
የቫለንቲና አባት ጁዋን ፓብሎ ኦሬላና የፖሊሶቹን እርምጃ በቸልተኝነት የተሞላ ሲሉ ወርፈውታል።
"እነዚህ ሁሉ ወንጀለኞች እስር ቤት እስካልገቡ ድረስ እስከ መጨረሻዋ ቀን ድረስ አላርፍም" ብለዋል።
የቺሊ ስደተኛ የሆኑት የቫለንቲና ቤተሰቦች ስለ ልጃቸው ሲናገሩ ስኬትቦርዲ ትወድ የነበረች እና አንድ ቀን የአሜሪካ ዜጋ እንደምትሆን ተስፋ አድርጋ ነበር።
አባቷ ለጋዜጠኞች ለገና ስጦታ የተገዛላትን የስኬትቦርድ ያሳዩ ሲሆን "ከመላእክት ጋር መንሸራተት እንድትችል ወደ መቃብር ስፍራዋ እወስደዋለሁ" ብለዋል።
"ልቤ ከሰውነቴ ተቀዶ የወጣ ይመስለኛል" ሲሉም አክለዋል።
"ለገና ቀን ላበረክትላት የገዛኋቸውን ስጦታዎች በገና ቀን ሲደርሱ ማየትን የመሰለ ህመም የለም" ብለዋል።