ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጥፋተኛ የተባለው ፖሊስ ወንጀሉን መፈጸሙን አመነ
በአሜሪካዋ የሚናፖሊስ ግዛት ጆርጅ ፍሎይድ የተሰኘው ጥቁር አሜሪካዊ አንገት ላይ ከ ዘጠኝ ደቂቃ በላይ በመንበርከክ ህይወቱ እንዲያልፍ ምክንያት የሆነው ፖሊስ ዴሪክ ቻውቪን የፍሎይድን የሲቪል መብት መጣሱን አመነ።
የ 45 ዓመቱ ፖሊስ በፍሎይድ ግድያ ከ22 ዓመታት በላይ ተፈርዶበት በእስር ላይ ይገኛል። ከአቃቤ ህግ ጋር እያደረገ ባለው የቅጣት ድርድር አማካኝነት ነው ትላንት ረቡዕ ከዚህ ቀደም ሰጥቶት የነበረውን የክሕደት ቃል ወደ እምነት ቃል ያሻሻለው።
በስምምነቱ መሰረትም በመጪው ወር ሊደረግ የነበረውን የክስ መስማት ሂደት የሚቀር ሲሆን የቅጣቱ መጠንም ዝቅ ይደረግለታል ተብሎ ይጠበቃል።
ግለሰቡ ሁለት ክሶች ቀርበውበታል። የመጀመሪያው ፍሎይድ እጁ በካቴና ታስሮ ባለበት ወቅት አንገቱ ላይ መንበርከክ ብሎም በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላም አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኝ ባለመርዳት ነው።
ግለሰቡ ከጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ባሻገርም እ.ኤ.አ. በ 2007 አንድ የ 14 አመት ታዳጊን በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት ስለጣሳቸው መብቶች ጭምርም የጥፋተኝነት ቃሉን ሰጥቷል።
የፖሊስ አባሉ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ ይግባኝ የጠየቀ ሲሆን በለይቶ ማቆያ ውስጥ ታስሮ እንዳለም ታውቋል። የሰጠው የጥፋተኝነት ቃሉ አሁን ካለው የእስር ግዜ በላይ ሊያረዝምበት እንደሚችል ይገመታል።
አቃብያነ ሕጉ ፖሊሱ ላደረሰው የሲቪል መብቶች ጥሰት ሕጎቹ እስከ 25 ዓመት ድረስ የሚደርስ የእስር ግዜ ጠይቀዋል። በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ወቅት የነበሩት ሌሎች ሁለት ፖሊሶችም በመጪው መጋቢት ወር ክሳቸው መሰማት ይጀምራል።