ፕሬዚዳንት ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ከዘር ማጥፋት ጋር አወዳደሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር በሃገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት የዘር ማጥፋት ይመስላል ብለዋል።
በሩሲያ የሚደገፉ አማፅያን ከዩክሬን ወታደሮች ጋር ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ እየተዋጉ ሲሆን ሩሲያ በጋራ ድንበር ላይ ጦሯን ማስፈሯ ውጥረቱን አንግሶታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዩክሬን አቻቻቸው ጋር ባደረጉት ንግግር ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ስለነበራቸው ውይይት ገልጸውላቸዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር አቅዳለች የሚል ስጋት ያለ ሲሆን ይህንን ግን ሩሲያ አትቀበለውም።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ፕሬዚዳንት ባይደንና ፕሬዚዳንት ፑቲን በስልክ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ውጥረቶችን ለማርገብ የተደረገ ሙከራም ተደርጎ ታይቷል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ ሩሲያ ዩክሬንን በድጋሜ የምታጠቃ ከሆነ ከባድ ማዕቀብ እንደምትጥል አስጠንቅቀዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን በፀብ አጫሪነት የከሰሰቻት ሲሆን በምስራቅ በኩል የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን አገሮች ድርጅት (ኔቶ) ጦር መስፋፋት ጋር በተያያዘም ሩሲያ ጦሯን ካሰማራችበት ድንበር እንዳይጠጋ በሚል ዋስትና ጠይቃለች።
የዩክሬን ባለስልጣናት እንዳሉት ሞስኮ በጥር ወር መጨረሻ ወታደራዊ ጥቃት ለማድረስ አቅዳለች ያሉ ሲሆን የአሜሪካ ባለስልጣናት በበኩላቸው ፕሬዚዳንት ፑቲን ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ግልፅ አይደለም ብለዋል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ሐሙስ ዕለት በሰጡት አስተያየት ከሩሲያ ድንበር ባሻገር በሩሲያ ተናጋሪዎች ላይ የሚደርሰውን አድልዎ ለመፍታት ያለመ ሲሆን አብዛኛዎቹ በምስራቃዊ ዩክሬን በዶንባስ ክልል ውስጥ ይኖራሉ።
በሩሲያውያን ላይ ያነጣጠረው ጥላቻ ለዘር ጭፍጨፋ የመጀመሪያው እርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል።
የግጭት ቀጠናውን በማጣቀስ "በዶንባስ የሚደረገውን አይተናል እናውቃለን" ያሉ ሲሆን "በእርግጠኝነት የዘር ማጥፋት ይመስላል" ብለዋል።












