በ104 ዓመታቸው ማንበብና መጻፍ ለመማር ትምህርት ቤት የገቡት ሕንዳዊት

የ104 ዓመቷ የዕድሜ ባለፀጋ ሕንዳዊት ለዘመናት ሲመኙት የነበረውን የማንበብና የመጻፍ ፍላጎት በዕድሜያቸው መጨረሻ ላይ ለማሳካት ቻሉ።
በደቡባዊ ሕንድ ኬራላ በምትባለው ግዛት ውስጥ ነዋሪ የሆኑት የ104 ዓመቷ አዛውንት ኩቲያማ ከልጅነታቸው ጀምሮ ትምህርት ቤት በመግባት ለመማር ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው።
እኚህ እናት ተምረው አስተማሪ የመሆን ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፤ ማንበብና መጻፍ ለማወቅ የትምህርት ቤት ደጅ ሳይረግጡ ይህ ምኞታቸውም ሳይሳካ ከ100 ዓመት በላይ ሲጠብቁ ቆይተዋል።
እናት ኩቲያማ በርካታ ታዳጊ ሴቶችን ከትምህርት ገበታ በሚያሰናክለው ያለዕድሜ ጋብቻ ውስጥ እንዲገቡ በመደረጋቸው የመማር ዕድልን ሳያገኙ ቆይተዋል።
ከትዳር በኋላ የህይወታቸው ዋነኛ ትኩረት የነበረው የቤት ውስጥ ሥራ ለመማር በነበራቸው ፍላጎት እንቅፋት ሆኖ፣ ፋታ በማይሰጠው የኩሽና፣ የቤት ውስጥ እንዲሁም እርሻ ሥራ ላይ ዘመናቸውን ገፍተው የትምህርት ብርሃንን ሳያዩ ቆይተዋል።
ነገር ግን ዕድሜያቸው መቶን ከዘለለ በኋላም የመማር ፍላጎታቸው ፈጽሞ አልቀዘቀዘም ነበር። በዚህ ወቅትም የህንድ መንግሥት በዘረጋው የመሠረተ ትምህርት መርሃ ግብር ውስጥ ገብተው ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል በውስጣቸው ተዳፍኖ የኖረውን የመማር ፍላጎት ለማሳካት ችለዋል።
በዚህም የ104 ዓመቷ እናት ኩቲያና ከልጅነታቸው ጀምረው ሲመኙት የነበረውን ማንበብና መጻፍ የማወቅ ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ ችለዋል።
መሠረታዊውን የማንበብና መጻፍ ክህሎትን ለመማር ወደ ትምህርት ቤት የሄዱት አዛውንት የልጅ፣ ልጅ፣ ልጆቻቸው ከሚሆኑ ታዳጊዎች ጋር ሆነው በደስታ ነበር የተማሩት።
የዕድሜ ባለፀጋዋ ኩቲያና ወደ ትምህርት ቤት የሄዱት እንዲሁ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በፍቅርና በትጋት ነበር ትምህርቱን የተከታተሉት።
የማንበብና የመጻፍ መሠረታዊ ትምህርቱን ተከታተለው ሲያጠናቅቁ በተሰጣቸው የመመዘኛ ፈተናም ጥሩ ውጤት ነበር ያገኙት። ከመቶ 89 ነጥብ በማግኘት ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።
አሁን የ104 ዓመቷ እናት በዕድሜያቸው መጨረሻ ላይ ለዘመናት ሲመኙት የነበረውን ማንበብና መጻፍ የማወቅ ፍላጎታቸውን በማሳካት የመቶ ዓመት ህልማቸውን እውን አድርገዋል።












