ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአካል እንቅስቃሴ እያደረገ የነበረውን ጥቁር የገደሉት ግለሰቦች ጥፋተኛ ሆነው ተገኙ
መንገድ ላይ የአካል እንቅስቃሴ እያደረገ የነበረን ጥቁር አሜሪካዊ የገደሉት ሶስት ነጮች ጥፋተኛ ሆነው ተገኙ።
የአህሙድ አርበሪ ግድያ የዘር ፍትህ ተቃውሞን በከፍተኛ ሁኔታ የቀሰቀሰ ጉዳይ ሆኗል።
በባለፈው አመት የካቲት ወር ነው ግሪጎሪ ማክሚካኤልና ትራቪስ ኤ ማክሚካኤል የተባሉ አባትና ልጅ ከጎረቤታቸው ዊልያም ብራያን ጋር ሆነው የ25 አመቱን አህሙድ ተኩሰው የገደሉት።
ተከሳሾቹ አህሙድን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሞከሩበት ወቅት እራሳቸውን ለመከላከል እርምጃ እንደወሰዱ ተናግረዋል። አቃብያነ ህግ በበኩላቸው በዘሩ ጥቃት እንደደረሰበት አስታውቀዋል።
ጥፋተኛ የሆኑት ግለሰቦች በትንሹ የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቃቸዋል።
በዋነኛነት በነጮች የተሞላው 12 አባላት ያሉት አቃብያነ ህግ (ጁሪ) ለ10 ሰዓታት ያህል ከተወያዩ በኋላ ረቡዕ እኩለ ቀን አካባቢ ለፍርድ ተመልሰዋል።
ሦስቱ ግለሰቦች በነፍስ ግድያ፣ አስከፊ ጥቃት በመፈጸም፣ በሃሰተኛ እስራትና ሆነ ብሎ በተፈፀመ ከባድ ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
በመጪው የካቲት ወርም ሶስቱ ግለሰቦች አህሙድ አርበሪን ጥቁር በመሆኑ ኢላማ አድርገዋል በሚል በፌደራል የጥላቻ ወንጀሎች ክስ ሌላ ፍርድ ይጠብቃቸዋል።
አህሙድ አርበሪ እንዴት ሞተ?
አህሙድ አርበሪ ጆርጂያ ውስጥ በምትገኘው ብሩንስዊክ የባህር ዳርቻ ከተማ ወጣ ብሎ ከሰዓት በኋላ በመሮጥ ላይ ነበር።
የአካባቢው ነዋሪ የሆነው ግሪጎሪ ማክሚካኤል ለፖሊስ እንደተናገረው አርበሪ በሴቲላ ሾርስ ከተማ ዳርቻ በተፈፀመ ተከታታይ የስርቆት ወንጀል ከጠረጠሩት ሰው ጋር መመሳሰሉን ነው።
ፖሊስ በበኩሉ ስለተባሉት ዘረፋዎች ምንም አይነት ሪፖርት እንዳልደረሰውና እና በአርበሪ ይዞታ ውስጥ ምንም አይነት የተሰረቀ ንብረት አልተገኘም ብሏል።
ትራቪስ ኤ ማክሚካኤልና ግሪጎሪ ማክሚካኤል ጠመንጃ ታጥቀው ምንም አይነት መሳሪያ ያልያዘውን አህሙድ አርበሪን በመኪና ውስጥ ሆነው በሰፈር ውስጥ እየተከታተሉ ያሳድድዱት ጀመር።
ከጥቂት ጊዜ በኋላም ጎረቤታቸው ብርያን የተባለ ግለሰብ ተቀላቅሎም ማሳደዳቸውን ቀጠሉ።
ግሪጎሪ ማክሚካኤል ድንገተኛ ጥሪ 911 የደወለ ሲሆን "እዚህ በሳቲላ ዳርቻ አካባቢ ነኝ። በመንገድ ላይ አንድ ጥቁር ወንድ እየሮጠ ነው" ሲል ይሰማል።
ትራቪስ ማክሚካኤል በበኩሉ ለችሎቱ በሰጠው ምስክርነት በመኪና ውስጥ እያሉ አህሙድን ሊያናግሩት እንደሞከሩና ምንም ምላሽ እንዳልሰጠም ገልጿል።
ከዚያም ከመኪናው ወርዶ ከአህሙድ ጋር እንደታገለና መተኮሱን ገልጿል። ትራቪስ ማክሚካኤል አህሙድ ሽጉጡን ሊቀበለው እንደሞከረ በመግለፅ ራሱን ለመከላከል መተኮሱን ተናግሯል።
አህሙድ የተገደለው በሶስት ጥይቶች ነው።
በአህሙድ ላይ በተደረገው የአስከሬን ምርመራ በደረቱ ላይ ሁለት ጊዜ እንደተተኮሰበትና በአንደኛው የእጅ አንጓው ውስጠኛ ክፍል ላይም መቁሰሉን ነው።
የ65 አመቱ ግሪጎሪ ማክሚካኤል፣ የ35 አመቱ ልጁ ትራቪስ እና ጎረቤታቸው የ52 ዓመቱ ዊልያም "ሮዲ" ብራያን በአውሮፓውያኑ ግንቦት 2020 በቁጥጥር ስር ውለዋል።
አቃቤ ህግ እንዳለው አህሙድ መሬት ላይ በወደቀበት ወቅት ዘሩን የሚያጣጥል እና ፀያፍ ነገሮችን ትራሺስ ማክሚካኤል መናገሩን አስረድቷል። ግለሰቦቹ ዘረኛ አይደለንም ይላሉ።