የቴስላ መኪና ባለቤቶች በመተግበሪያ ችግር መኪናቸውን መክፈት አልቻሉም ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርካታ ቴስላ የተሰኘውን መኪና የሚያሽከረክሩ ሰዎች መኪናውን የሚያንቀሳቅሰው መተግበሪያ ችግር ካጋጠመው በኋላ መኪናቸውን መክፈት አለመቻላቸውና ከውጭ እንደተቆለፋበቸው እየተናገሩ ነው።
የቴስላ አሽከርካሪዎች በማሕበራዊ ድር አምባ ገፆቻቸው የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያው እየሠራ እንዳልሆነ መልዕክት እንደደረሳቸውና መኪናቸውን መሾፈር እንዳቃታቸው ፅፈዋል።
የቴስላ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢላን መስክ በትዊተር ገፁ "እያጣራን ነው" ብሎ ከፃፈ በኋላ መተግበሪያው ሥራ መጀመሩን ተናግሯል።
የቴስላ መተግበሪያ ልክ እንደ መኪና ቁልፍ አሽከርካሪዎች መኪናቸውን እንዲከፍቱና እንዲያስነሱና የሚያስችል ነው።
ይህ መተግበሪያ ሥራ ማቆሙ ግራ ያጋባቸው የመኪናው ባለቤቶች ብስጭታቸውን ሲገልፁ ነበር።
"ከቤቴ አንድ ሰዓት ርቀት ላይ መኪናዬ አልሠራ ብሎኝ ቆሜያለሁ" ሲል አንድ ግለሰብ ትዊተር ላይ ለጥፏል።
ቢያንስ 500 የቴስላ አሽከርካሪዎች አርብ ምሽት 3፡40 ገደማ በመተግበሪያው ምክንያት መኪናቸው አልሠራ ብሏቸው እንደቆሙ አሳውቀው ነበር።
ከአምስት ሰዓታት በኋላ ግን 60 ሰዎች ብቻ አሁንም መተግበሪያው አልሠራ እንዳላቸው ጥቆማ አድርሰዋል።
"ይቅርታ፤ ይህ ድጋሚ እንዳይፈጠር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን" ሲል የቴስላ መሥራች ኢላን መስክ ፅፏል።
መተግበሪያው መኪናውን ለመክፈትና ለማስነሳት የምንጠቀምበት ብቸኛው መንገድ አይደለም ሲሉ ዘ ካር ኤክስፐርት የተሰኘው ድረ-ገፅ አርታዒ ስቱዋርት ሜሶን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"መኪናን ለማስነሳትም ሆነ ለመክፈት አሊያም ለመዝጋት ሌላ መንገድ ይኖራል። ነገር ግን ችግር የሚሆነው አሽከርካሪዎችን ይህንን ከረሱ ነው" ይላሉ አርታዒው።
"ቴክኖሎጂ ነገሮችን ቀለል ያደርጋል፤ ነገር ግን ሁሌም መቶ በመቶ የሚሠራ 'ሰርቨር' ላይ ጥገኛ ነው። ለምሳሌ በስልኬ እከፍላለሁ ብዬ የባንክ ካርዴን ቤቴ ጥዬ እንደመውጣት ነው። ሁልጊዜም አንድ አማራጭ ላይ ጥገኛ የምንሆን ከሆነ በመጥፎ አጋጣሚ ልንያዝ እንችላለን።"
በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪያው ላይ ጥናት ያደረጉት የበርሚንግሃም ቢዝነስ ስኩል ፕሮፌሰሩ ዳቪድ ቤይሊ የቴስላ አሽከርካሪ ሲሆኑ አርብ ዕለት ያጋጠመው ክስተት ገፈት ቀማሽ ነበሩ።
"በአንድ በኩል ቴስላ የራሱ ስኬት ተጠቂ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
"ደንበኞቹ ድርጅቱ የፈጠራቸውን ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀሙ ያበረታታሉ። ነገር ግን ይህ ቴክኖሎጂ አንዳንድ ጊዜ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል።"
"እርግጥ ነው ቁልፍ መጠቀም ይቻላል። ነገር ግን አብዛኛዎቹ የቴስላ ባለቤቶች ቴክኖሎጂ ላይ ጥገኞች ናቸው።"












