ዩናይትድ ኪንግደም ሃማስን ሽብርተኛ ቡድን ስትል ልትፈርጅ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩኬ ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል ሃገራቸው የፍልስጥኤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስን ሽብርተኛ ቡድን ስትል እንምትፈርጅ አስታውቀዋል።
ጋዛን የሚቆጣጠረው የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ በፊትም ቢሆን በዩናይትድ ኪንግደም አሸባሪ ቡድን ተብሏል።
ነገር ግን አሁን ዩኬ ሃማስን በጠቅላላው አሸባሪ ቡድን ማለቷ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን ሊጎዳው ይችላል ተብሏል።
የቡድኑ አባል መሆን፣ ድጋፍ መስጠትና ማሰባሰብ እንዲሁም የቡድኑን አጀንዳ የሚያንፀባርቅ ልብስ መልበስ ወንጀል ነው።
ይህን ድርጊት ሰፊፅሙ የተገኙ ሰዎች እስከ 14 ዓመት እሥራት እንዲሁም የገንዘብ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል።
የዩናይትድ ኪንግደም የሕዝብ እንደራሴዎች አባላት በጉዳዩ ላይ ከመከሩ በኋላ ረቂቅ ሐሳቡ ከፀደቀ ከ5 ቀናት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል።
ሃማስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶችን እስራኤል ላይ የፈፀመ ሲሆን ግጭት በተነሳባቸው ጊዜዎች በርካታ ሚሳዔሎችንም ተኩሷል ተብሎ ይወቀሳል።
እስራኤል ከግብፅ ጋር በመጣመር በጋዛ ሠርጥ የሚገኘውን ሃማስ ለመደምሰስ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝራለች።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እስራኤልም ሆነች ሃማስ የመብት ጥሰት ፈፅመዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።
ሚኒስትሯ ይህን የሃማስን ሽብርተኛ የመባል ዜና ያሰሙት ዋሺንግተን ውስጥ ስለደህንነት ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።
"ሃማስ ከባድ ሽብር የማድረስ ኃይል ያለው ቡድን ነው። በጣም ዘመናዊ የሆኑ መሣሪያዎች ባለቤት ነው። የሽብርተኞች ማሠልጠኛ ተቋም አለው፤ ከዚህ በፊትም የሽብር ጥቃት ፈፅሞ ያውቃል" ብለዋል ሚኒስትሯ።
በምላሹ ሃማስ ዩናይት2 ኪንግደም "በንፁሃን ደም ስም ወራሪዎችን እየደገፈች ነው" ሲል ወቅሷል።
እስራኤል ዜናውን "በጣም አስፈላጊ ውሳኔ" ስትል በደስታ ተቀብላዋለች።
ፓርላማው የሚኒስትሯን ሓሳብ ካፀደቀ ሃማስ፤ ዩናይት ኪንግደም ሽብርተኛ ቡድን ስትል ከፈረጀቻቸው 78 ቡድኖች መካከል አንዱ ይሆናል።
ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ሕብረት ሃማስን ሽብርተኛ ቡድን ብለው ከፈረጁት ቆይተዋል።












