ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሁለት ሰዎችን ተኩሶ የገደለው ወጣት ከወንጀል ነጻ መባሉ ባይደንን አስቆጣ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ዓመት በዊስኮንሲን የዘር ግጭት ወቅት ሁለት ሰዎችን በጥይት የገደለው ታዳጊ ነጻ መባሉ እንዳስቆጣቸው ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ የዳኞችን ውሳኔ እንደሚደግፉ ለጋዜጠኞች ከተናገሩ በኋላ በጽሑፍ መግለጫቸው ፍርዱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
የ18 ዓመቱ ካይል ሪተንሐውስ ነሐሴ 25/2020 በኬኖሻ ከተፈጸሙ ወንጀሎች በሙሉ ነጻ መሆኑ ሲገለጽ ሲያለቅስ ታይቷል።
አሜሪካን የከፋፈለውን የፍርድ ውሳኔ በመቃወም አነስተኛ ተቃውሞዎች ነበሩ።
ከሦስት ቀን ተኩል ችሎት በኋላ ሰባት ሴቶች እና አምስት ወንዶችን ያካተተው የዳኞች ቡድን ውሳኔውን ሲያሳልፍ ሪተንሐውስ በእፎይታ ሊወድቅ ተቃርቦ ነበር። እናቱ ዌንዲም ስታነባ ታይታለች።
የቀድሞ ወጣት ምልምል ፖሊስ ከሁለት የግድያ ወንጀል፣ ከአንድ የመግደል ሙከራ እና ከሁለት ደኅንነትን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ክሶች ነው ነጻ የተባለው።
ሪተንሐውስ የ36 ዓመቱን ጆሴፍ ሮዘንባም እና የ26 ዓመቱን አንቶኒ ሁበርን መግደሉን እና የ28 ዓመቱ ጊዬጅ ግሮስክሬቱዝን ማቁሰሉን አምኗል። ሆኖም እራሴን ለመከላከል የፈጸምኩት ነው ሲል ተከራክሯል።
ተከሳሹ እና ተጎጂዎቹ በሙሉ ነጮች ናቸው። ድርጊቱ የተፈጸመው በፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ምክንያት በተፈጠረ ግርግር ወቅት በመሆኑ የዘር ጉዳይ ከክስተቱ ጋር ተያይዟል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ባይደን በትዊተር ገጻቸው ላይ ምንም ማስረጃ ሳይሰጡ ሪተንሐውስን ከነጭ የበላይነት አራማጆች ጋር ያገናኘ የሚመስል ቪዲዮ ለቀዋል።
አርብ ዕለት ከዋይት ሐውስ በር ላይ አንድ ጋዜጠኛ ፕሬዝዳንቱን ስለ ታዳጊው የሰጡትን አስተያየት አሁንም ስለመደገፋቸው ጠይቋቸው ነበር።
ባይደንም "ዳኞች የወሰኑትን እደገፋለሁ። የዳኝነት ሥርዓቱ ይሠራል እና እሱን ማክበር አለብን" ብለዋል።
በኋላ ላይ ባወጡት መግለጫ "በኬኖሻ የተሰጠው ፍርድ እኔንም ጨምሮ ብዙ አሜሪካውያን እንዲናደዱ እና እንዲጨነቁ ቢያደርግም የዳኞች ውሳኔን መቀበል አለብን" ብለዋል።
በኬኖሻ ምን ሆነ?
ፖሊሶች ጃኮብ ብሌክ የተባለ ጥቁር ግለሰብን ነሐሴ 23/2020 ከጀርባው ሰባት ጊዜ በጥይት ይተኩሱበታል።
ኬኖሻ ከተማ ለሁለት ቀናት በብጥብጥ፣ በዝርፊያ እና በእሳት ቃጠሎ ከተናወጠች በኋላ በወቅቱ 17 ዓመቱ የነበረው ሪተንሐውስ ወደ ስፍራው ያቀናል።
ጠበቆቹ ወጣቱ "ጥሩ አስተሳሰብ ያለው ታዳጊ" በሚል ገልጸው ወደ ሚድዌስተርን ያቀናው የግል ንብረትን ለመጠበቅ መሆኑንና ለሕይወቱ በመፍራት ሰዎቹን ላይ ተኩሷል ብለዋል።
ዐቃቤ ሕጉ በበኩሉ ሪተንሐውስን "ግዴለሽ" ያለው ሲሆን ጉዳት ያደረሰባቸው ሰዎች ጀግኖች ሲል ከመግለጽ ባለፈ "እየተኮሰ" ነው ብለው ያሰቡትን ሰው ትጥቅ ለማስፈታት ሲሞክሩ ነበር ሲል ገልጿል።
ሮዘንባም በዚያ ምሽት የተሳሳተ እርምጃ ሲወስድ እና ሽጉጡን ለመያዝ ከመሞከሩ በፊት ሪተንሐውስን እንዳሳደደው ለችሎቱ ተገልጿል። ሪተንሐውስም ተኩሶ ገድሎታል።
ሁበር የተገደለው ሪተንሐውስን ጭንቅላቱን ወይም አንገቱን በስኬትቦርድ ከመታ በኋላ ነው።
ግሮስክሬቱዝን ሽጉጡን ወደ ሪተንሐውስ ከደገነ በኋላ ነበር ተተኩሶ ጉዳት የደረሰበት።
ምን አስተያየት ተሰጠ?
ከፍርዱ በኋላ ጠበቃው ማርክ ሪቻርድስ ደንበኛቸው "ሕይወቱን መቀጠል ይፈልጋል" ብለዋል።
"ይህ እንዳይፈጠር ምኞቱ ነበር። ሲመሰክር እንደተናገረው ጉዳዩን እሱ አልጀመረም።"
የሁበር ወላጆች በፍርዱ "ልባችን ተሰብሯል" ብለዋል።
ካረን ብሉም እና ጆን ሁበር በመግለጫቸው "ታጣቂ ሰዎች በየትኛውም ከተማ ተገኝተው ብጥብጥ እንዲቀሰቀስ በማድረግ በፈጠሩት አደጋም ሰዎች ላይ በመተኮስ እንደማምለጫ ማቅረባቸው ተቀባይነት የሌለውን መልዕክት እንዲያስተላልፍ ያደርጋል" ብለዋል።
ከችሎቱ ውጨ የተሰበሰቡ ጥቂት ተቃዋሚዎች "ገዳዩ ካይል ሪተንሐውስ" እና "ፍትሕ ከሌለ ሰላም የለም" የሚል መፈክር በመያዝ ተሰብስበው ነበር ተብሏል።
ውሳኔው መሰጠቱ ከተማዋ ወደፊት እንድትራመድ ያግዛል ሲሉ የአካባቢው የመደብር ባለቤቶች ደስታቸውን ገልጸዋል።
ችሎቱ የፖለቲካ መከፋፈሎችን አጋልጧል። ብዙ ዲሞክራቶች ፍርዱን ሲያወግዙ ሪፐብሊካኖች 'ፍትሕ ሰፈነ' ሲሉ ተደምጠዋል። አንዳንዶቹም የሥራ ዕድል ሰጥተውታል።
ፍርዱን ተከትሎ የፎክስ ኒውሱ ተከር ካርልሰን ከሪተንሐውስ ጋር ካደረገውና ሰኞ ከሚተላለፈው ቃለ መጠይቅ ላይ ቅንጫቢውን ለቋል።
በቃለ መጠይቁ ላይ ሪተንሐውስ ስለተፈጠረው ነገር በሚያየው "አስፈሪ" ህልሞች የተነሳ ሌሊት በቀዝቃዛ ላብ ተጠምቆ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ገልጿል።