በማልኮም ኤክስ ግድያ የተፈረደባቸው ሁለት ሰዎች ክሳቸው ውድቅ ሊሆን ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ ነባር የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ሕግ፤ በፈረንጆቹ 1965 አሜሪካዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማልኮም ኤክስን ገድለዋል የተባሉት ሁለት ሰዎች ክስ ውድቅ ሊሆን እንደሚችል ተናገሩ።
ሙሐመድ አዚዝና ኻሊል ኢስላም የሚገባቸውን ፍትህ አላገኙም ብለዋል የማንሃታን ቀጠና አቃቤ ሕግ።
አቃቤ ሕግ ሳይረስ ቫንስ ጁንዬር ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት ኤፍቢአይና ፖሊስ ሁለቱን ሰዎች በቁጥጥር ሥር ለማቆየት የሚያስችል በቂ ማስረጃ የላቸውም።
ማልኮም ኤክስ በቤተሰቦቹ ፊት ኒውዮርክ ውስጥ ባለ አንድ አነስተኛ አዳራሽ ውስጥ ነበር የተገደለው።
አዚዝና ኢስላም እንዲሁም አንድ ሶስተኛ ሰው ማልኮም ኤክስን ገድለዋል ተብለው የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸው ነበር።
የኔሽን ኦፍ ኢስላም አባላት የሆኑት ሶስቱ ሰዎች በአመክሮ ተለቀዋል። ኢስላም ከ12 ዓመታት በፊት ሕይወቱ አልፏል።
ከኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቃቤ ሕጉ ቫንስ በሕግ አስከባሪዎች ስም አዚዝና ኢስላምን ይቅርታ ጠይቀዋል።
"ይህ የሚያመላክተው ሕግ አስከባሪዎች ባለፉት ዘመናት አልፎ አልፎም ኃላፊነታቸው በአግባቡ አለመጣታቸውን ነው" ብለዋል።
"እኚህ ሰዎች የሚገባቸውን ፍትህ አላገኙም።
አቃቤ ሕጉ በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከሆን ዘርዘር ያለ መረጃ ሐሙስ ዕለት ይፋ ይሆናል።
ባለፈው ዓመት የማንሃታን ቀጠና አቃቤ ሕግ ኢነሰንስ ፕሮጀክት በተሰኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት አማካይነት የሁለቱን ሰዎች ክስ መልሶ እንዲያጤነው ተደርጎ ነበር።
ድርጅቱ በሃስት ክስ ተመስርቶባቸው ብይን የተሰጣቸው ሰዎችን ለማገዝ የተቋቋመ ነው።
ከጥቂት ወራት በፊት የማልኮም ኤክስ ሴት ልጆች አዲስ ማስረጃ መገኘቱን ተከትሎ ክሱ አንደ አዲስ እንዲከፈት ጠይቀው ነበር።
አዲስ ማስረጃ የአንድ በወቅቱ ፖሊስ የነበረ ሰው ሲሆን ሞት አፋፍ ላይ ሳለ በፃፈው ደብዳቤ የማልኮም ኤክስን የ1965 ግድያ ያቀነባበሩት ኤፍቢአይና ፖሊስ ናቸው ይላል።
ግርማ ሞገስ የከበበው ማልኮም ኤክስ ለጥቁር አሜሪካዊያን ነፃነት ይታገል የነበረ መንፈሰ ጠንካራ ሰው ነበር።
ኔሽን ኦፍ ኦስላም የተሰኘው ኃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ድርጅት ቀንደኛ ቃል አቀባይ ሆኖ ለረዥም ዓመታት ያገለገለው ማልኮም በ39 ዓመቱ ነው የተገደለው።












