በኬንያ እስረኞች ማምለጣቸውን ተከትሎ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ተባረሩ

መሃመድ አሊ

የፎቶው ባለመብት, Mohamed Ali Abikar

ታትሟል

ከሽብር ወንጀል ጋር በተያያዘ ተፈርዶባቸው የነበሩ ሶስት እስረኞች ከፍተኛ ጥበቃ ካለው እስር ቤት ማምለጣቸውን ተከትሎ የኬንያ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ከስልጣናቸው ተባረሩ።

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በሰጡት መግለጫ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ዊክሊፍ ኦጋሎ "በሁሉም የፀጥታ አካላት አመራር አካላት ውስጥ ተጠያቂነትን ለማስፈን" በአፋጣኝ ይተካሉ ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ በተጨማሪም የፀጥታ ኤጀንሲዎች በሙሉ ያመለጡ እስረኞችን አሳዶ ለመያዝ "ያለውን ሃብት ሁሉ" እንዲጠቀሙ መመሪያ ሰጥተዋል።

ከማረሚያ ቤት ካመለጡት መካከል በአውሮፓውያኑ 2015 በጋሪሳ ዩኒቨርስቲ 148 ሰዎች በተገደሉበት ጥቃት የተከሰሰው መሃመድ አሊ ይገኝበታል።

መሃመድ አሊ በተከሰሰበት ወንጀል የ41 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ሁለተኛው ግለሰብ በአውሮፓውያኑ 2012 በኬንያ ፓርላማ ላይ ያልተሳካ ጥቃት በማቀነባባር እና ሶስተኛው ግለሰብ ደግሞ በሶማሊያ የሚገኘውን የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ለመቀላቀል ሲሞክር በቁጥጥር ስር የዋለ ነው።

ባለሥልጣናቱ ሶስቱን እስረኞች ለማግኘት በሚደረገው ጥረት መረጃ ለሰጠ ማንኛውም ግለሰብ 20 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም 178 ሺህ ዶላር ሸልማት ይሰጣል በሚል ለህዝቡ አቤቱታ አቅርበዋል።