አስትራዜኒካ ከሚያመርተው የኮሮናቫይረስ ክትባት ትርፍ መሰብሰብ ሊጀምር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አስትራዜኒካ የሚያመርተውን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ያለትርፍ ለአገራት የሚሰራጭበትን አሠራር ሊቀይር እንደሆነ ተሰምቷል።
ግዙፉ መድኃኒት አምራች ኩባንያ ከቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑ ተከታታይ የንግድ ስምምነቶች የተፈራረመ ሲሆን ከክትባቱ ሽያጭ መጠነኛ ገቢ እንደሚያስገባ አስታውቋል።
ሆኖም ኩባንያው ለድሃ አገራት ክትባቱን ያለትርፍ ማቅረቡን እንደሚቀጥል ገልጿል።
ኩባንያው ከዚህ ቀደም ከክትባቱ ገንዘብ ለማግኘት አቅዶ የነበረው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት መሆኑ ካበቃ በኋላ ነው።
የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓስካል ሶሪዮት፤ ወረርሽኙ ወደተወሰኑ አከባቢዎች እየጠበበ መምጣቱን ተናግረዋል።
"ቀደም ሲል ያለምንም ትርፍ ክትባቱን ለማቅረብ የወሰነው ዋናው ዓላማችን የዓለምን ጤና መጠበቅ ስለነበር ነው" ብለዋል።
"ምንም እንኳን በተለያዩ አገራት የፖለቲካ ትችቶችን ብናስተናግድም ከተፎካካሪዎች በተቃራኒ ትርፍ ለማግኘት አለመሥራታችን ምንም አይነት ፀፀት አላስከተለብንም" ሲሉ ሥራ አስፈጻሚው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረገ ትብር የበለጸገው ክትባቱ በዓለም ዙሪያ የአንድ ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት መታደግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።
"በፍፁም አልፀፀትምም። እንደ ኩባንያ እኛ በሠራነው ሥራ ኩራት ይሰማናል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አድነናል። የአስተራዜኒካ ቡድን ጥሩ ሥራ መሥራቱን ቀጥሎበታል" ሲሉም አክለዋል።
ከክትባቱ ሽያጭ ከፍተኛ ገቢ እንደማይጠበቅ የገለጹ ኃላፊው፤ ክትባቱ በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረቡን ለማረጋገጥ ለአገራት በየደረጃው የዋጋ ተመን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
እስከዚህ የፈረንጆቹ ዓመት መገባደጃ ድረስ አስትራዜኒካ 250 ሚሊዮን ክትባቶችን በኮቫክስ መርሐ ግብር አማካይነት ለታዳጊ አገራት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።
ፋይዘር እና ሞደርናን ጨምሮ ሌሎች የክትባት አምራቾች ከምርቶቻቸው ትርፍ እያገኙ ያገኛሉ።
በመድኃኒት ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው መደበኛ የትርፍ ጣሪያ 20 በመቶ መሆኑን የሚገልጹት ሶሪዮት፤ የኮቪድ-19 ክትባት ግን አንድ ብልቃጥ 5 ዶላር የሚሸጥ በመሆኑ አስተራዜኒካ አነስተኛ ትርፍ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።
'ግሎባል ጀስቲስ ናው' የተሰኘ እንቅስቃሴ ዳይሬክተር ኒክ ዴርደን በበኩላቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቀጠለበት በዚህ ወቅት አስትራዜኒካ ከክትባቱ ትርፍ ለማግኘት መወሰኑ ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ ውሳኔውን ተቃውመዋል።












