በኔዘርላንድስ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመቀነስ ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለ

ታትሟል

የኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩት በአገራቸው የክረምት መግባትን ተከትሎ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ለሦስት ሳምንታት የመገበያያ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እና ምግብ አቅራቢዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ እገዳ መጣሉን ገለጹ።

ይህም በምዕራብ አውሮፓ የመጀመሪያዋ ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለች አገር አድርጓታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጨናቂ እና ከባድ ውሳኔ ነው ያሉት እገዳ፤ መነሻው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እና ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ነው ብለዋል።

ሆኖም የአገሪቱን መንግሥት ውሳኔ ተቃውመው አደባባይ የውጡ ዜጎች ታይተዋል። በዚህም ሳቢያ ፖሊስ በሄግ በመቶዎች በሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ውሃ ረጭቷል።

በአሁኑ ወቅት በበርካታ የአውሮፓ አገራት የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየጨመረ ሲሆን ለዚህ ከተሰጡ ምክንያቶች አንዱ በብዙ አገራት ክትባት በብዛት እየተወሰደ አለመሆኑ ነው።

በኔዘርላንድስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ክትባት ማግኘቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሦስት ሳምንቱ ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በኔዘርላንድስ ባለፈው አርብ የተመዘገበው ዕለታዊ የኮቪድ-19 አሐዝ 16 ሺህ 287 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ያመላክታል።

ይህ ቁጥር ከሐሙስ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ቢሆንም ካለፈው ሳምንት ጋር ሲወዳደር ግን በአንድ ሦስተኛ ከፍ ያለ ነው።

የኔዘርላንድስ የክትባት ምጣኔ በአንጻራዊነት ከፍተኛ የሚባል ነው። በአገሪቱ ከ12 ዓመት በላይ ካሉ ሰዎች 82.4 በመቶ የሚሆኑት ሁለት ዙር የወረርስኙ መከላከያ ክትባት ያገኙ ሲሆን፤ ይህም ከጠቅላላው ሕዝብ 73 በመቶውን የሚይዝ ነው።