ለ26 ዓመታት በስህተት የታሰረው አሜሪካዊ በይቅርታ ተፈታ

ታትሟል

አሜሪካ ውስጥ በተሳሳተ የፍርድ ሂደት በሰው መግደል ወንጀል ተከሶ የተፈረደበት ግለሰብ ከ26 ዓመት እስር በኋላ አስሩ በስህተት የተፈጸመ ነው ተብሎ ተለቀቀ።

ዳንቴ ሻርፕ በተሳሳተ የፍርድ ሂደት ምክንያት እስር የተፈረደበት ከ26 ዓመታት በፊት ነበር።

አሜሪካ፣ ኖርዝ ካሮላይና የተወለደው ዳንቴ ከግድያ ወንጀል ጋር በተያያዘ ነበር በስህተት እስራት የተፈረደበት።

እአአ በ1994 እስኪፈረድበት ድረስ ወንጀሉን አለመፈጸሙን ለማሳመን ብዙ ጥረት አድርጓል።

ጥረቱ ሳይሳካ ለ26 ዓመታት በእስር ከቆየ በኋላ እአአ ነሐሴ 2019 ነጻነቱን አግኝቷል።

"የጠለሸው የቤተሰቦቼ ስም ንጹህ ሆኗል። እኔ እና ቤተሰቦቼም ሸክማችን ቀሏል" ሲል ለጋዜጠኞች ተናግሯል።

ዳንቴ በስህተት እንደታሰረ ከታወቀ በኋላ ከእስር እስኪለቀቅ ድረስ አንድ ዓመት ጠብቋል። ምንም እንኳን የታሰረው በስህተት እንደነበረ ቢደረስበትም የይቅርታ ሂደቱ ድፍን ዓመት ወስዷል።

ቢቢሲ ስለ ታራሚዎች እና የፍትሕ ሥርዓት መዛባት በሠራው ዘጋቢ ፊልም ከዳሰሳቸው ጉዳዮች አንዱም ነው።

ታራሚዎች ነጻነታቸውን ለማግኘት ለረዥም ጊዜ መጠበቅ ግዴታ ይሆንባቸዋል።

የኖርዝ ካሮላይና አገረ ገዢ ሮይ ኩፐር እንደሚሉት፤ ልክ እንደ ዳንቴ በስህተት የታሰሩ ሰዎች ይቅርታ ሲደረግላቸው ሕዝቡ ማወቅ አለበት።

ዳንቴ ከእስር የተለቀቀው በይቅርታ ስለሆነ በስህተት ለታሰረባቸው 26 ዓመታት ካሳ መጠየቅ ይችላል።

"በስህተት ተፈርዶባቸው እስር ቤት ያሉ ሰዎች ነጻ እስከሚወጡ ድረስ የእኔ ነጻነት ሙሉ አይሆንም" ይላል ዳንቴ።

"እስር ቤት ሳለሁ ብዙ ንጹህ ሰዎች ገጥመውኛል። ሰዎች በስህተት እንዳይታሰሩ ሲባል የፍትሕ ሥርዓቱ መለወጥ አለበት" ሲልም አክሏል።

ዳንቴ በኖርዝ ካሮላይና የፍትሕ ሥርዓት እንዲሻሻል ንቅናቄ የሚያደርገው ፎርዋርድ ጀስቲስ ቡድን አባል ነው።

ከ26 ዓመት በፊት እስር የተፈረደበት ጆርጅ ራድክሊፍ የተባለን ግለሰብ ገድለሀል ተብሎ ነበር። ያኔ ምስክርነት ከሰጡ መካከል አንድ ታዳጊ ኋላ ላይ የምስክርነት ቃሏን ብትቀይርም ዳንቴ ነጻ አልወጣም።

ነጻ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስም 26 ዓመታት ወስዷል።

የፍትሕ ሥርዓቱን መቀየር

ዳንቴ ቀሪ ሕይወቱን ማሳለፍ የሚፈልገው የአሜሪካን የፍትሕ ሥርዓት በማረም እንደሆነ ይናገራል።

እአአ ከ1989 ወዲህ ከ2,887 በላይ ሰዎች በስህተት መታሰራቸውን የአሜሪካ ብሔራዊ መረጃ ይጠቁማል። እነዚህ ሰዎች ያለአግበባብ ማረሚያ ቤት የቆዩበት ዓመት ቢደመር ወደ 25,000 ይጠጋል።

ዳንቴ በነጻ እንዲቀቅ ከተወሰነ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው የኖርዝ ካሮላይና አገረ ገዢ ሮይ ኩፐር የይቅርታ ደብዳቤውን የፈረሙት።

የዳንቴ ጠበቃ ካትሊን ስዌን እንደምትለው፤ ዳንቴ የገጠመው ውጣ ውረድ የፍትሕ ሥርዓቱ መቀየር እንዳለበት ጠቋሚ ነው።

ዳንቴን ነጻ ለማውጣት የዓመታት ትግል አስፈልጓል። ታዋቂ ጠበቆች፣ ቤተሰቦቹ፣ የቤተ ክርስቲያን ፓስተሮች እና ሌሎችም ለነጻነቱ ታግለዋል።

ዳንቴ ነጻነቱን አግኝቶ ከቤተሰቦቹ ጋር ቢቀላቀልም ልክ እንደሱው በስህተት የታሰሩ ሰዎችን ነጻ ካላወጣ እስከወዲያኛው እረፍት እንደማያገኝ ይናገራል።

"የፍትሕ ሥርዓታችን የተዛባ ነው። መቀየር አለበት" ይላል።