ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕን የዋይት ሐውስ ሰነዶች መርማሪዎች እንዲመለከቱ ፍርድ ቤት ፈቀደ
አንድ የአሜሪካ ዳኛ የካፒቶል አመጽን ከትትሎ ምርመራ የሚያደርገው የኮንግረስ ኮሚቴ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዋይት ሐውስ ሰነዶችን እንዲመለከት ፈቃድ ሰጡ።
ትራምፕ ሰዶቹን መርማሪ ኮሚቴው እንዳይመለከተው ያስችለኛል ያሉትን ሕጋዊ መብት አንስተው ተከራክረው ነበር።
ምርመራውን የሚያካሂደው ኮሚቴ ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ መንግሥት ምክር ቤት ህንጻ (ካፒቶል ሂል) ላይ ባለፈው ዓመት ጥር ወር የተካሄደውን አመጽ ቀደመው ያውቁ ነበር የሚለውን ለመለየት ለሚያደርገው ጥረት መልስ ለማግኘት ነው።
የአሜሪካ ኮንግረስ በምርጫ ያሸነፉትን የጆ ባይደንን ፕሬዝደንትነት ለማጽደቅ በተቀመጠበት ወቅት የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሂል ላይ ወረራ መፈጸማቸው ይታወሳል።
ትራምፕ ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ምርመራ እያካሄደ የሚገኘው ኮሚቴ በኮንግረሱ ላይ በትራምፕ ደጋፊዎች ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት የዋይት ሐውስ የስልክ ልውውጦች እና ትራምፕ ከማን ጋር ተገናኝተዋል ነበር የሚለውን ለማወቅ ነው ስነዶቹን የሚመለከተው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ደግሞ ሰነዶቹ ለማንም ይፋ እንዳይሆኑ ሲቃወሙ ነበር።
ነገር ግን ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ታንያ ቹትካን ማክሰኞ ዕለት የዋይት ሐውስ ሰነዶችን የሚጠብቀው ብሔራዊ የማህደር መስሪያ ቤት ትብበር እንዲያደርግና ሰነዶቹን ለመርማሪ ኮሚቴው እንዲሰጥ አዝዘዋል።
ዳኛ ታንያ በቀድሞው ፕሬዝዳነት ባራክ ኦባማ የተሾሙ ሲሆን የዶናልድ ትራምፕን ጥያቄም ውድቅ አድርገዋል።
"ፕሬዝዳንቶች እኮ ንጉሥ አይደሉም። ቅሬታ ያቀረቡት ግለሰብም አሁን ላይ ፕሬዝዳንት አይደሉም" ብለዋል ዳኛዋ ታንያ ባስተላለፉት ባለ 39 ገጽ የውሳኔ ሀሳብ። ነገር ግን ይህ ውሳኔ ወደ ፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንደሚሄድ ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስ 16 የዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ረዳቶች ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ታዘዋል።
ከእነዚህም መካከል የቀድሞ የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ኬይሊ ማክናኒ፣ የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት ስቴፈን ሚለር፣ የቀድሞ የቅስቀሳ ኃላፊው ቢል ስቴፈን፣ የቀድሞ የዋይት ሐውስ ከፍተኛ ኃላፊ ማርክ ሚዶውስ እና የቀድሞ የፕሬዝዳንቱ የደኅንነት አማካሪ ማይክል ፍሊን ይገኙበታል።
ከካፒቶል ሂል ጥቃት ጋር ተያይዞ እስካሁን ድረስ 670 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በወቅቱም አንድ የካፒቶል ሒል የፖሊስ አባልን ጨምሮ አምስት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።