ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ ኪንግደም ዜጎቿ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ አሳሰበች
ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጠውን ግጭት ተከትሎ ዜጎቿ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ አሳሰበች።
ከዚህ በተጨማሪም የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ከሚደርጉጓቸው የትኛውም አይነት ጉዞዎች እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
የዩኬ መንግሥት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት አማጺያን መካከል የሚደረገው ጦርነት በፍጥነት እና ምንም አይነት የማስጠንቀቂያ መልክት ሳይታይ ሊባባስ ይችላል ብሏል።
ከዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ እና ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ለማድረግ የወጣን እቅድ በአንክሮ እንዲመረምሩ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ማሳሰቢያ ከሰጡ አገራት መካከል አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እስራኤል፣ ስዊድን፣ ቤልጄም፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሩሲያ ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አፍሪካዊቷ አገር ዛምቢያ በኢትዮጵ ያሉ ዜጎቿን ማስወጣቷን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሃካይንዴ ሂቺሌማ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረው፣ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለተደረገላቸው ትብብር አመስግነዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የዩናይትድ ኪንግደም ፓስፖርት የያዙ ሰዎች አሃዝ በትክክል ባይታወቅም፤ ከኢትዮጵያ ለመውጣት ፍላጎት ያላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሊሆን እንደሚሉ ባለሥልጣናት ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ላይ፤ በቀጣይ ቀናት "ከኢትዮጵያ ለመውጣት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ብሏል"፤ ለዚህም ዜጎቹ "የንግድ በረራ አማራጮች እስካሉ ደረስ" ከኢትዮጵያ እንዲወጡ መክሯል።
የዩኬ መንግሥት "የፖለቲካ እና የደኅንነት ሁኔታ አሳሳቢ በሚሆንበት ጊዜ፤ ኤምባሲው ሊሰጥ የሚችለው አገልግሎት የተገደበ ሊሆን ይችላል" በማለት በአስቸጋሪ ወቅት ዜጎች መንግሥት አገልግሎት ይሰጠናል ብለው መተማመን እንደሌለባቸው አሳስቧል።
የውጭ አገራት መንግሥታት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ማሳሰብ የጀመሩት የኢትዮጵያ መንግሥት በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ እና የህወሓት አማጺያን የደቡብ ወሎ ከተሞችን ተቆጣጠረው ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ፍላጎት እንዳላቸው ካስታወቁ በኋላ ነው።
አንድ ዓመት የሞላው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ተባብሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋ ሲሆን በተለይ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ በተለያዩ ቦታዎች ከባድ ውጊያዎች እተካሄዱ ነው።
ይህንንም ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱና የክልል አስተዳደሮች የአማጺያኑን እንቅስቃሴ ለመመከት ለሕዝቡ ጥሪ አቅርበዋል።