ዩኬ ዐሣ የማጥድ መብት ላይ በገባት ቅሬታ የፈረንሳይ አምባሳደርን ጠራች

ታትሟል

ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ሕብረት ከወጣች በኋላ ባለው የዐሣ ማጥመድ መብት ላይ በተፈጠረ አለመስማማት ከፈረንሳይ የሚሰነዘረውን "ምክንያታዊ ያልሆነ" ዛቻ በማውገዝ በዩኬ የፈረንሳይ አምባሳደር ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠራች።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ በዩናይትድ ኪንግደም የፈረንሳይ አምባሳደር ካትሪን ኮሎናን "ተገቢ እና ተመጣጣኝ ያልሆኑ ስጋቶችን" እንዲያብራሩ ጠይቀዋል።

ትላንት የፈረንሳይ መንግሥት አንድ የዩናይትድ ኪንግደም ዐሣ አጥማጅ መረከብን የያዘ ሲሆን ሌላ የዩኬ መርከብ ላይ ደግሞ ቅጣት ጥሏል።

የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ቅጣት የተጣለባት ዐሣ አጥማጅ መርከብ ፈቃድ እንደሌላት ገልጸዋል።

ሆኖም የዩኬ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ጆርጅ ኤውስስቲስ የአውሮፓ ሕብረት ለመርከቧ ፈቃድ መስጠቱን ተናግረው መርከቧ ፈቃድ ከተሰጣቸው መርከቦች ዝርዝር ውስጥ የወጣችበት ምክንያት "ግልጽ አይደለም" ብለዋል።

ፈረንሳይ በበኩሏ ከብሬግዚት ስምምነት በተቃነ መልኩ ዩኬ ለበርካታ የፈረንሳይ ዐሣ አጥማጅ መርከቦች ፈቃድ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለችም ትላለች።

ዩኬ ከብሬግዚት ስምምነት በተቃራኒ በርካታ ዐሣ አጥምዳለች በሚል ፈረንሳይ ባለፈው ወር ቁጣዋን አሰምታ ነበር።

በዚህም ምክንያት እስከ ቀጣዩ ወር ሁለተኛው ቀን ይህ ጉዳይ እልባት የማያገኝ ከሆነ ከተለያዩ ወደቦች የዩኬ ጀልባዎችን እና እቃ ጫኝ ተሽከርካሪዎችን እንደምታግድ ፈረንሳይ አስጠንቅቃለች።

በተጨማሪም ፈረንሳይ በብሪታኒያ ውስጥ ለምትገኘው ጀርሲ የኤሌክትሪክ አቅርቧትን እንደምታቋርጥም ስተገልጽ ነበር።

የፈረንሳይ ሚንስትር ከሌመነት ቤውን "ኃይለ ቃል መጠቀም አለብን። ምክንያቱም በሚያሳዝን ሁኔታ የብሪታንያ መንግሥት የሚረዳው ያንን ብቻ ነው" ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

የዩኬ መንግሥት በበኩሉ በፈረንሳይ መንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ፍትሐዊነት የሚጎድላቸውና ከአውሮፓ ሕብረት የንግድ ስምምነት ብሎም ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር የሚቃረኑ ናቸው ብሏል።

"በዚህ ጉዳይ የፈረንሳይ መንግሥት በተከታታይ እየተጠቀመ ያለው አገላለጽ ችግሩን ለመፍታት ከባድ ያደርገዋል" ሲሉ የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስተያየታቸውን ሰንዘረዋል።