አሜሪካ ከካናዳ እና ሜክሲኮ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ልትከፍት ነው

አሜሪካ ድንበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አሜሪካ ከሜክሲኮ እና ካናዳ ጋር በምትጋራቸው የየብስ ድንበሮች በኩል ሙሉ ክትባት የወሰዱ ተጓዦች ከሕዳር ወር ጀምሮ መግባት እንደሚችሉ ገልጻለች።

በየበስ እና በባህር ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው የቆየው ወሳኝ ስራ ያላቸው ተጓዦች የነበሩ ሲሆን ይህ እገዳ እንደሚነሳ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮ ደግሞ ድንበሮቹን አቋርጦ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገባ ማንኛውም ተጓዥ የኮቪድ 19 ክትባት ማረጋገጫ መያዝ ይጠበቅበታል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት አሜሪካ ከፈረንጆቹ መጋቢት 2020 ጀምሮ ከሰሜን እና ከደቡብ ጎረቤቶቿ የሚነሱ ተጓዞች ድንበሯን እንዳያቋርጡ እገዳ ጥላ ነበር።

ነገር ግን የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በቅርቡ ሙሉ በሙሉ የተከተቡና ወደ ሀገሪቱ ለሚገቡ ተጓዦች ከቀጣዩ ወር ጀምሮ የተጣለው ገደብ እንደሚቀልላቸው አስታውቆ ነበር።

አሁን ያሉት መመሪያዎች ባለፉት 14 ቀናት በዩናይትድ ኪንግደም፣ በቻይና፣ በሕንድ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በኢራን፣ በብራዚል እና በበርካታ የአውሮፓ አገራት ውስጥ የነበሩና የአሜሪካ ያልሆኑ ዜጎች ድንበሩን አቋርጠው እንዳይገቡ ይከለክላል።

የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊው አሌሃንድሮ ከንቲካስ በሰጡት መግለጫ መምሪያቸው "መደበኛ ጉዞን በአስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ለመቀጠል በማስቻሉን ስገልጽላችሁ በደስታ ነው" ብለዋል።

ሆኖም ግን ውሳኔው ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆኑ የተባለ ነገር የለም።