ሕንድ በኮቪድ-19 ለሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች ካሳ ልትከፍል ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሕንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መንግሥት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ህይወታቸው ላለፈ ሰዎች ቤተሰቦች እከፍለዋለው ያለውን ካሳ ማጽደቁ ተሰምቷል።
ለእያንዳንዱ ሟች የሚከፈለው የካሳ መጠን ደግሞ 50 ሺ ሩፒ ወይም 647 ዶላር መሆኑ ተገልጿል።
በሕንድ እስካሁን ባለው ይፋዊ መረጃ መሰረት 447 ሺ ዜጎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት የሟቾች ቁጥር መንግስት ከሚለው በአስር አጥፍ ሊበልጥ ይችላል።
የሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኃላፊው ኤምአር ሻህ ሰኝ ዕለት ''የሟቾች ወራሽ አልያም የቅርብ ዘመድ ካሳውን ያገኛል'' ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ አክሎም የሟቾች ቤተሰቦች ተገቢውን ማስረጃና ሰነድ ለመንግሥት ካስገቡ በኋላ በሚቀጥሉት 30 ቀናት ውስጥ የካሳ ክፍያውን ከመንግስት ማግኘት ይችላሉ ብሏል።
ባለፈው ሰኔ ወር ጠበቆችና የመብት ተቆርቋሪዎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ እንዲሳተፍና በኮቪድ-19 ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ሰዎች ካሳ እንዲከፈል ፊርማ አሰባስበው ነበር።
በወቅቱም የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ብሄራዊ አደጋ ተብሎ ከታወጀ ለተጎጂዎች መንግሥት ካሳ የመክፈል ግዴታ እንዳለበት የብሄራዊ አደጋ አመራር መመሪያን በመጥቀስ ተከራክረዋል።
መመሪያው እንደሚለው በማንኛው ብሄራዊ አደጋ ወቅት ተጎጂዎች ከመንግስት እስከ 400 ሺ ሩፒ የሚደርስ ካሳ ሊከፈላቸው እንደሚገባ ተጠቅሷል።
"መንግስት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ገንዘብ እንዳወጣ እናውቃለን። ነገር ግን በመመሪያው መሰረት መንግስት 400 ሺ ሩፒ ለተጎጂዎች መክፈል ነበረበት። ወይም ደግሞ ለደሃ ማህበረሶች ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን መስጠትና ደህና ኑሮ ላላቸው ደግሞ ዝቅተኛውን መስጠት ይቻል ነበር" ብለዋል ፊርማውን ሲያሰባስቡ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ጋወራቭ ባንሳል።
የፌደራል መንግስት እንደሚለው የካሳ ክፍያው የሚፈጸመው በኮቪድ-19 ምክንያት የቤተሰብ አባል ለሞተባቸው ሰዎች ሲሆን ግለሰቡ አልያም ግለሰቧ በቫይረሱ ምክንያት ስለመሞታቸው ደግሞ ተገቢው ማስረጃ መቅረብ አለበት።
የካሳ ክፍያውን የሚፈጽሙት ደግሞ የግዛት መንግስታት ናቸው ተብሏል።
ኬራላ እና ራጃስታን የተባሉት ግዛቶች ደግሞ የካሳ ክፍያው ከፍተኛ ጫና እንደሚያደርስባቸው በመግለጽ የፌደራሉ መንግስት ክፍያውን እንዲፈጽም ጠይቀዋል።
እንደ ካርናታካ ያሉት ግዛቶች ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች እስከ 100 ሺ ሩፒ የሚደርስ የካሳ ክፍያ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። እስካሁን 16 ቤተሰቦች የካሳ ክፍያውን እንዳገኙ የአካባቢው ገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።












