በዩናይትድ ኪንግደም የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎልን ለመፍታት የጦሩ አባላት ሊሰማሩ ነው

ታትሟል

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት የጦር ሠራዊቱ አባላት ከሰኞ ጀምሮ በአገሪቷ ለሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ ማድረስ እንደሚጀምሩ አስታወቀ።

100 አሽከርካሪዎችን ጨምሮ ወደ 200 የሚጠጉ ወንድ እና ሴት የሠራዊቱ አባላት በነዳጅ ማደያዎቹ ያለውን የነዳጅ እጥረት ለማቃለል በጊዜያዊነት ማቅረብ ይጀምራሉ ተብሏል።

ሚኒስትሮች 300 የሚሆኑ ከአገር ውጪ ያሉ የነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች አሽከርካሪዎች እስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ በዩኬ ውስጥ መሥራት እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

በዚህ ሳምንት በአገሪቱ የአሽከርካሪዎች እጥረት የነዳጅ አቅርቦትን ካስተጓጎለ በኋላ በነዳጅ ማደያዎች ረዣዥም ሰልፎች ታይተዋል።

ሰዎች መደበኛ ፍጆታቸውን ያህል ብቻ ቢገዙ በቂ ነዳጅ መኖሩን የገለፁት ሚኒስትሮቹ፤ እስካሁን ከተሸጠው በላይ የነዳጅ ክምችት በመኖሩ በነዳጅ ማደያዎች ያለው ሁኔታ ይሻሻላል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች ከሌሎቹ አካባቢዎች በባሰ ክፉኛ መቸገራቸውን ገልጸዋል።

አርብ ዕለት አርኤሲ ሞተሪንግ ግሩፕ ምንም እንኳን በበርካታ ቦታዎች የአቅርቦት ችግር ቢኖርም የተፈጠረው መስተጓጎል ግን እየቀለለ ነው ብሏል።

ሆኖም አሽከርካሪዎች ለቅዳሜ እና እሁድ ነዳጅ ስለሞሉ አነስተኛ የነዳጅ ማደያዎች ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸው አስረድቷል።

በዩናይትድ ኪንግደም ካሉት 8 ሺህ 300 የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ 5 ሺህ 500 የሚሆኑትን የሚወክለው የነዳጅ ቸርቻሪዎች ማኅበር ራሳቸውን የቻሉ ነዳጅ ቸርቻሪ አባላቱ ላይ እምብዛም ለውጥ አለመኖሩን ገልጿል።

ማኅበሩ በመላው ዩኬ ውስጥ በ1ሺህ 100 ጣቢያዎች ላይ ባደረገው ጥናት 26 በመቶ የሚሆኑት ነዳጅ ወይም ናፍጣ የሌላቸው ሲሆን ሐሙስ ዕለትም እጥረቱ ወደ 27 በመቶ ዝቅ ብሏል።

የጦር ሠራዊቱ አባላት ለዚሁ አላማ ሥልጠና እየወሰዱ ሲሆን የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት በመላ አገሪቱ ነዳጅ ማቅረብ እንደሚጀምሩ መንግሥት አስታውቋል።

የመከላከያ ኃላፊ ቤን ዋላስ እንዳሉት ሠራተኞቹ ከአሽከርካሪዎች ጋር በመሆን ነዳጅ ማቅረብ ይጀምራሉ።

"በዩኬ የነዳጅ እጥረት የለም። በመሆኑም ሰዎች እንደተለመደው ነዳጅ መሸመት ይችላሉ። በቅርቡ ወደ ለመድነው የግዢ እና የሽያጭ ሂደት እንመለሳለን" ብለዋል ቤን ዋላስ።

ችግሩን ለማቃለል 300 ለሚሆኑ የነዳጅ ቦቴ አሽከርካሪዎች በዩኬ በጊዜያዊነት እንዲሰሩ ከመፍቀድ በተጨማሪም 4 ሺህ 700 ለሚሆኑ የምግብ ምርት አቅራቢ አሽከርካሪዎች ጊዜያዊ ቪዛ ተሰጥቷቸዋል።

እነዚህ አሽከርካሪዎች ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ የካቲት መጨረሻ ድረስ የሚቆዩ ናቸው ተብሏል።

ከዚህም ባሻገር ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ለሚቆዩ 5 ሺህ 500 ለሚሆኑ የዶሮ እርባታ ሠራተኞች ጊዜያዊ ቪዛ ተሰጥቷል።