ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰሜን ኮሪያ አዲስ የፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤል ሙከራ አደረገች
ሰሜን ኮሪያ ሐሙስ ዕለት አዲስ የፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን የገለጸች ሲሆን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አራተኛ የጦር መሣሪያ ሙከራዋ ሆኖ ተመዝግቧል።
ሰሜን ኮሪያ አዲሱን ሙከራዋን ያደረገችው የኒውክሌር አቅም እንዳለው የሚታመነውን አዲስ የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሙከራ ካደረገች ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሙከራዎቹ "አለመረጋጋትን እና አለመተማመንን የበለጠ ይፈጥራሉ" ብለዋል።
ፒዮንግያንግ የጦር መሣሪያው ራስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ መሆናቸውን በመግለጽ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያን "ፍትሐዊ ያልሆነ አቋም ይዘዋል" በማለት ወንጅላለች።
ሙከራዎቹ ምንም እንኳን ጥብቅ ማዕቀቦች ቢኖሩም ፒዮንግያንግ የጦር መሣሪያ መሥራቷን ለማዘግየት ፍላጎት እንደሌላት የሚያሳይ ግልፅ ምልክት ተደርገው ተወስደዋል።
በመንግሥታዊው የዜና ማሰራጫ ኬሲኤንኤ መሠረት አዲሱ የፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤል "አስደናቂ አፈፃፀም" ያሳየ ሲሆን "አዳዲስ ቁልፍ ቴክኖሎጂዎችን" አካቷል ሲል ዘግቧል።
ሙከራው የተደረገው የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ከደቡብ ኮሪያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ወደነበረበት መመለስ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።
ኪም የአሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎን ከሰዋል። " አሜሪካ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በማታለል የጥላቻ ድርጊቱን ለመደበቅ ሞክራለች" ብለዋል።
አንዳንድ ተንታኞች ፒዮንግያንግ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ግንኙነቷን በማስቀጠል አሜሪካን በማስወጣት ዋሽንግተን እና ሴኡልን ለመለያየት እንደምትፈልግ አመላካች ነው ብለው ያምናሉ።
ሆኖም ሰሜን ኮሪያ የማዕቀብ እፎይታን እና ሌሎች ድጋፎችን አሜሪካ እንድታደርግላት የደቡብ ኮሪያን ድጋፍ ትፈልጋለች።
ሰሜን ኮሪያ ከዓለም ተቆራርጣ ከአንድ ዓመት በላይ አሳልፋለች።
ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ከቅርብ አጋሯ ከቻይና ጋር አብዛኛውን ንግዶች አቋርጣለች። በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ የምግብ እጥረት አሳሳቢ ነው ተብሎ ይታሰባል።
በመጋቢት ወር አገሪቱ ማዕቀቦችን ወደ ጎን በማለት የባልስቲክ ሚሳኤሎችን ሞክራለች። ይህም ከአሜሪካ፣ ከጃፓን እና ከደቡብ ኮሪያ ጠንካራ ወቀሳ አስነስቶባታል።
ባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት የአቶሚክ ኤጀንሲ ሰሜን ኮሪያ "በጣም አሳሳቢ" ያለውን ለኒዩክሌር መሣሪያዎች የሚረዳ ፕሉቶኒየም ማምረት የሚችል ማብላያዋን እንደገና እንደጀመረች ገልጿል።