ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአፍሪካ የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ
የዓለም ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ በቀጣይ ሳምንታት በአፍሪካ የነዳጃ ዋጋ በተመሳሳይ ሊጨምር እንደሚችል ባለሙያዎች አመለከቱ።
ትናንት ማክሰኞ የአንድ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 80 የአሜሪካ ዶላር ደርሶ ነበር። ይህም ከሦስት ዓመት ወዲህ የተመዘገበ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ነው ተብሏል።
ዓለም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጫናዎች መላቀቅ ስትጀምር የምጣኔ ሐብት እንቅስቃሴዎች እየተነቃቁ ነው። ይህን ተከትሎም የነዳጅ ፍላጎት ጣራ እየነካ ነው።
የዘርፉ ባለሙያዎች አሁን ላይ ለታየው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አንዱ ምክንያት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የምጣኔ ሐብት እንቅስቃሴዎች መጨመሩ ነው ይላሉ።
የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ፓትሪክ ኦባታ፤ የነዳጅ ፍላጎቱ በተለየ በአሜሪካ እና አውሮፓ እየጨመረ ስለሚቀጥል የዋጋ ጭማሪው ለወራት ሊዘልቅ እንደሚችል ያስረዳሉ።
በዚህም ምክንያት ነዳጅ አምራች ያልሆኑ አገራት የኃይል ምንጫቸውን ፍላጎት ለማስተካከል በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ሊያደርጉ ይችላሉ ይላሉ።
ሌላኛው የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ኬን ጊቺንጋ፤ በምጣኔ ሐብት እድገት ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ሚና ስላለው የነዳጅ ዋጋ ሲጨመር የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋም አብሮ ይጨምራል በማለት ያስረዳሉ።
የነዳጅ አምራች እና ላኪ አገራት ጥምረት የሆነው ኦፔክ በቀጣይ ሳምንት ይመክራል ተብሏል።
የኦፔክ አባላት በቀጣይ ሳምንት ውይይታቸው የነዳጅ አቅርቦትን መጠን ከፍ ለማድረግ ከውሳኔ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ማይክል ፋሞሮቲ በቀጣይ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው የነዳጅ መጠን በኦፔክ አባላት የሚወሰን ይሆናል ይላሉ።
ነዳጅ አምራች እና ላኪ አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ተከትሎ ተቀዛቅዞ የነበረውን የነዳጅ አቅርቦት መጠን፤ አምራች አገራት የምርት መጠናቸውን ከፍ እንዲያደርጉ በመፍቀድ የነዳጅ ዋጋ እንዲረጋጋ ሊያደርጉ ይችላሉ ሲሉ ይተነብያሉ።
"ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ኦፔክ ጠንከር ያለ እርምጃ ይወስዳል ብዬ እጠብቃለሁ" ብለዋል የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ማይክል ፋሞሮቲ።