በጦር መሳሪያ ግዢ ምክንያት ፍጥጫ ውስጥ የገቡት ቱርክና አሜሪካ

ታትሟል

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቱርክ አቻቸው ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ዛሬ ሩሲያ ውስጥ ተገናኝተው ይነጋገራሉ።

ሁለቱ መሪዎች ከሚመክሩባቸው ጉዳዮች መካከል የጦር መሳሪያ ግዢ እና የሶሪያ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳዎች ይሆናሉ ተብሏል።

ቱርክ ከሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን መግዛቷ ከአሜሪካ ጋር ውዝግብ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።

"አሜሪካ ክለከላ ማድረግ አትችልም"

ቱርክ ከሩሲያ ለመግዛት ያሰብኩትን ጦር መሳሪያ በተመለከተ አሜሪካ ምንም አይነት ክልከላ ልታደርግ አትችልም ስትል የአሜሪካንን አቋም ተቃውማለች።

የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ቱርክ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስልታዊ የሚሳኤል ሥርዓቶችን ከሩሲያ ለመግዛት እቅድ እንዳላት አስታውቀዋል።

ፕሬዝደንት ኤርዶሃን አገራቸው ለሁለትኛ ዙር ኤስ-400 ከምድር ወደ ሰማይ የሚወነጨፉ ሩሲያ ሠራሽ ሚሳኤሎችን ለመግዛት በዝግጅት ላይ መሆኗ በታወቀበት ጊዜ አሜሪካ ተቃውሞ አሰምታለች።

በዚህም ሳቢያ ቱርክ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አጋሯ አሜሪካ ጋር ውዝግብ ውስጥ የከተታት ሲሆን ተጨማሪ ማዕቀብ ሊያስጥልባት ይችላል ተብሏል።

አሜሪካ ሩሲያ ሰራሾቹ ኤስ-400 ሚሳኤሎች ለኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶቼ ስጋት ናቸው ትላለች። ከዚህ በተጨማሪም ዋሽንግተን ሚሳኤሎቹ ለኔቶ የድንበር መከላከያ ሥርዓት አደጋ ናቸው ትላለች።

ቱርክ በበኩሏ የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን አጥጋቢ በሆነ መልኩ ከኔቶ አባል አገራት መግዛት እንዳልቻለች በማመልከት ከሩሲያ ጋር ስምምነት ላይ እንደደረሰች ገልጻለች።

"ሊኖረን ስለሚችለው የጦር መሳሪያ ዓይነት ከየትኛውም አገር በየትኛውም ደረጃ ማንም ጣልቃ መግባት አይችልም" ሲሉ ፕሬዝደንት ኤርዶሃን በአሜሪካው ሲቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ በቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል።

"በዚህ ላይ ማንም ጣልቃ መግባት አይችልም። እንዲህ አይነት ውሳኔ የምንሰጠው እኛ ብቻ ነን" በማለት ኤርዶሃን የአሜሪካንን አቋም ተችተዋል።

ከወራት በፊት ቱርክ የመጀመሪያወን ዙር ኤስ-400 ሚሳኤሎችን ከሩሲያ መግዛቷን ተከትሎ አሜሪካ የቱርክ መከላከያ ኢንደስትሪ ዳይሬክቶሬት ኃላፊ እሰማኢል ዴሚር እና ሦስት የተቋሙ ሠራተኞች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

ከዚህ በተጨማሪም ቱርክ ተመሳሳይ የጦር መሳሪያ ግዢ የምትፈጽም ከሆነ ሌላ ማዕቀብ እንደሚጣልባት አሜሪካ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።

"በየትኛውም ደረጃ ቱርክ ኤስ-400 የሚሳኤል ሥርዓቶችን እንዳትይዝ ወይም የትኛውንም አይነት ሩሲያ ሰራሽ ጦር መሳሪያዎችን ከመግዛት እንድትቆጠብ እናሳስባለን" ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አሳስበዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም አሜሪካ ቱርክን እንደ ወዳጅ አገር ነው የምትመለከታት ካሉ በኋላ፤ አለመግባባት ውስጥ ሆነን እንኳ ግንኙነታችንን ማጠናክር ነው የምንፈልገው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ቱርክ ሁለተኛውን ዙር ኤስ-400 ሚሳኤሎችን የምትረከብበትን መንገድ በተመለከተ ከሩሲያ ጋር ንግግር እያደረገች ትገኛለች።

ኤርዶሃን ዛሬ በሩሲያ ተገኝተው ከፕሬዝደንት ቭላድረሚር ፑቲን ጋር በሚያደርጉት ውይይት ዋነኛ ጉዳያቸው ኤስ-400 ሚሳኤሎች እና በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ያለው ግጭት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ቱርክ እና ሩሲያ የው ፖሊሲ አቋም

ቱርክ እና ሩሲያ የወዳጅነታቸውን ያህል ፍላጎታቸውን ለየቅል እንደሆነ በሚያሳዩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ይመራሉ።

ቱርክ እና ሩሲያ በሶሪያ ጉዳይ የተለያየ ፍላጎት ነው ያላቸው። ሁለቱ አገራት በሶሪያ በተቃራኒ ጎራ የቆሙ ኃይሎችን ይደግፋሉ። ቱርክ የሶሪያውን ፕሬዝደንት ባሻር አል-አሳድን ከሥልጣን ለመግልበጥ የሚታገሉትን ኃይሎች ትደግፋለች። ሩሲያ በበኩሏ አሳድ በስልጣን እንዲቆዩ ድጋፍ ታደርጋለች።

ቱርክ እና ሩሲያ ከዚህ ቀደም በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ በሚገኘው ኢድሊብ ግዛት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተጥሷል እያሉ አንዳቸው ሌላኛው ላይ ጣት ሲቀስሩ ነበር።

ሞስኮ ሶሪያ የገባሁት በአሳድ መንግሥት ይፋዊ ጥሪ ነው በማለት በጦርነት የምትታመሰውን አገር መልሶ ለመገንባታ የቱርክ ጣልቃ ገብነት እንቅፋት መሆኑን ስትጠቅስ ነበር።

ቱርክ በበኩሏ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ከጎረቤት አገር ወደ ቱርክ እየተሻገሩ ስለሆነ፤ የቀጠናውን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በሰሜን ሶሪያ አሰማርታ በአሳድ መንግሥት ላይ የተነሱ ወታደሮችን ትደግፋለች።

ቱርክ በአሁን ወቅት ወደ 3.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ሶሪያዊያን ስደተኞችን አስጠልላ ትገኛለች።

ቱርክ እና ሩሲያ በሊቢያ ያላቸው አቋምም የተለያየ ነው።

ቱርክ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠውን መንግሥት ስትደግፍ፤ ዋግነር የተሰኘው ቅጠረኛው የሩሲያ ቡድን ደግሞ ለተቃዋሚው ጀነራል ኻሊፋ ሃፍጣር ጦር ይዋጋል።

በአንድ ወቅት የኻፍጣር ጦር ትሪፖሊን ለመቆጣጠር ከጫፍ በደረሰ ወቅት ቱርክ ባሰማራቻቸው ወታደሮች ተገፍቶ እንዲሸሽ ሆኗል።

ከሶሪያ በተጨማሪም ቱርክ እና ሩሲያ በሦስተኛ አገር ጉዳይ ጣልቃ ገብተው አቋማቸው ለየቅል የሆነበት አጋማጣሚም አልጠፋም።

ከወራት በፊት በተካሄደው የአዘርባጅን እና የአርሜኒያ ጦርነት ቱርክ እና ሩሲያ የተለያየ ጎራን ደግፈው ቆመው ነበር።

ቱርክ በዚህ ጦርነት አዘርባጃን በድል እንድትወጣ ቱርክ ሰራሹን ባይራክታር ቲቢ2 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) ጥቅም ላይ አውላ ነበር።

ቱርክ ከወራት በፊት ለዩክሬን ድሮኖችን መሸጧ ሩሲያን ያበሳጨ ጉዳይም ነበር።

ቱርክ እና ሩሲያ ወዳጅነት

ምንም እንኳ ቱርክ እና ሩሲያ በሶሪያ፣ ሊቢያ፣ በአርሜኒያ-አዘርባጀን ጦርነት እንዲሁም በዩክሬን ጉዳይ ያላቸው አቋም ይለያይ እንጂ በጦር መሳሪያ ግዢ፣ ኢነርጂ እና ቱሪዝም መስኮች ጠንካራ ግንኙነት መመስረት ችለዋል።

ቱርክ ከሩሲያ ከፍተኛ መጠን ያለውን ጋዝ የምታስገባ ሲሆን በተቃራዊው ቱርክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሩሲያ ጎብኚዎችን በየዓመቱ በማስተናገድ ጠቀም ያለ ገንዘብ ታገኛለች።