የኬንያና የደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች በትብብር ለመስራት ተስማሙ

ከአንድ ዓመት በኋላ በረራ የጀመረው የደቡብ አፍሪካ ኤር መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከአንድ ዓመት በኋላ በረራ የጀመረው የደቡብ አፍሪካ ኤር መንገድ
ታትሟል

የደቡብ አፍሪካና የኬንያ አየር መንገዶች አህጉራዊ አየር መንገድ ለመመስረት ያላቸውን የወደፊት ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ።

በተከታታይ በገጠማቸው ኪሳራና አስተዳደራዊ ችግሮች ሳቢያ እየተፈተኑ ያሉት ሁለቱ አየር መንገዶች አሁን የሚፈጥሩት ትብብር በአፍሪካ የአየር ጉዞ ዘርፍ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ያስችላቸዋል ተብሏል።

ሥራውን አቋርጦ የነበረው የደቡብ አፍሪካው አየር መንገድ ወደ በረራ ከተመለሰ በኋላ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው ከኬንያ አቻው ጋር የትብብር ስምምነት ላይ የደረሰው።

ሁለቱ አየር መንገዶች በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ላይ ያላቸውን የዕድገት አቅም በጋራ ለማሳደግ አቅደዋል።

የኬንያ እና የደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች አሁን በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት በቀዳሚነት የጉዞ መስመሮችን በጋራ በማካሄድ፣ የአውሮፕላን ጥገናና የአገልግሎት አቅርቦታቸውን መጠን በመጨመር ትርፋማነታቸውን ለማሳደግ ተስማምተዋል።

ሁለቱ አየር መንገዶች እንዳሉት አሁን ያደረጉት ስምምነት ትብብር እንጂ ውህደት እንዳልሆነ በመግለጽ በዚህም በተመሳሳይ ከሌሎች አየር መንገዶች ጋር በጋራ ለመስራት ነጻ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በኪሳራ ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ ሥራውን አቁሞ የነበረው የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ከሳምንት በፊት ነው መልሶ በረራ የጀመረው።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሥራው ክፉኛ የተጎዳበት የኬንያ አየር መንገድ ኪሳራውን ለመቀነስ ሲል በጭነት ማመላለስ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጫና ካሳደረባቸው ዘርፎች መካከል የአየር ትራንስፖርት አንዱ ሲሆን በመላው ዓለም የሚገኙ አየር መንገዶችን ለኪሳራ ከመዳረጋቸው በተጨማሪ በርካቶች ሠራተኛ ከመቀነስ አንስቶ አስከመዘጋት ደርሰዋል።

በአፍሪካም በርካታ አየር መንገዶች ከበረራ ውጪ ለመሆን የተገደዱ ሲሆን የደቡብ አፍሪካና የኬንያ አየር መንገዶችም ከፍተኛ ኪሳራ አጋጥሟቸዋል።

በአፍሪካ ውስጥ ግዙፉ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በገቢው ላይ ከፍተኛ ቅናሽ ቢያጋጥመውም አሁንም በዘርፉ የአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ በመሆን ቀጥሏል።