አነጋጋሪዎቹ ከፌስቡክ ያፈተለኩት አምስት ምስጢሮች

ታትሟል

በተገባደደው ሳምንት ዋል ስትሪት ጆርናልን ጨምሮ ሌሎች የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የፌስቡክን የውስጥ አሠራር የተመለከቱ እና ከተቋሙ ያፈተለኩ ሰነዶችን ይዘው ወጥተዋል።

አብዛኛው መረጃ በፌስቡክ ውስጥ በሚሠሩ ግለሰቦች የወጣ ሲሆን፤ ይህም በውስጡ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ጭምር የሚገኙ የመረጃ ጠቋሚዎች እንዳሉ ያመላከተ ነው ተብሏል።

እነዚህ ከፌስቡክ ያፈተለኩት የውስጥ ሰነዶች መንግሥት ብሎም ተቆጣጣሪ ተቋማት ምርመራዎችን እንዲያካሂዱ የሚረዱ በርካታ መረጃዎችን የያዙ ናቸውም ተብሏል።

ይሁንና ፌስቡክ የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ አስተባብሏል።

ለመሆኑ ባለፈው ሳምነት ይፋ የሆኑት አምስት ነገሮች ምንድናቸው?

ታዋቂ ሰዎችን በተለየ ሁኔታ መያዝ

ለዋል ስትሪት ጆርናል የሾለከው መረጃ እንደሚያሳየው በርካታ ዝነኞች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም በርካታ ተከታይ ያላቸው የፌስቡክ ተጠቃሚዎች 'ኤክስ ቼክ' ወይም 'ክሮስ ቼክ' የሚባል የተለየ ሥርዓት ተዘርግቶላቸዋል። ይህ ሥርዓት የሚያጋሩትን መረጃ የሚያስተዳድር ነው።

ፌስቡክ ይህንን ሥርዓት የሚጠቀምበት መንገድ ላይ የቀረበበትን ትችት ቢቀበልም ይህ ሥርዓት አንድ የተለጠፈ መረጃ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚፈልግ ሲሆን የሚጠቀምበት ሂደት መሆኑን ገልጿል።

"ይህ የማኅበረሰብ አንቂዎች ስለ አንድ ጥቃት መረጃ መስጠት ሲፈልጉ ወይም ጋዜጠኞች ግጭት ካለበት ቦታ ሆነው ሲዘግቡ የምንጠቀመው አይነት ስልት ነው" ሲል ፌስቡክ ራሱን ተከላክሏል።

ዋል ስትሪት ያወጣቸው ሰነዶች ጊዜያቸው ያለፈባቸውን እና የቆዩ መረጃዎች በማገጣጠም ዋናውን ነጥብ ለመሸፈን የተደረገ ጥረት ነው ሲልም ወቅሷል።

ፌስቡክ አክሎም በክሮስ ቼክ አጠቃቀም ላይ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት እና እነሱንም ለማሻሻል እየሠራሁ ባለሁበት ወቅት ነው ይህ መረጃ የወጣው ብሏል።

ምንም እንኳን ተቋሙ ራሱን ቢከላከልም የፌስቡክ ተቆጣጣሪ ቦርድ ግን ተጨማሪ ግልጽነት እንዲኖር ጠይቋል።

ቦርዱ አክሎም "እነዚህ ዘገባዎች ድርጅቱ ውሳኔዎችን በሚሰጥበት ግዜ የሚከተለው ወጥ ያልሆነ አሠራር የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ያደረጉ ናቸው" ብሏል።

ቦርዱ ፌስቡክ በዚህ ክሮስ ቼክ በተባለው ሥርዓት ላይ ጥርት ያለ መረጃ የማይኖር ከሆነ ግን ፌስቡክ በፖለቲካዊ እና የንግድ ግምቶች ጫና ስር ወድቋል ለሚሉት ክሶች የበለጠ የሚያጋልጠው ይሆናል ሲልም አስጠንቅቋል።

ይህ በራሱ በፌስቡክ የተዋቀረው ተቆጣጣሪ ቦርድ ሥራውን ከጀመረ ወዲህ ድርጅቱ ፖሊሲዎቹን ሊያሻሽል ይገባዋል ባለባቸው 70 ጉዳዮች ላይ ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል።

ፌስቡክ ባለው የላላ አቋም ከሠራተኞቹ የመጡ ጥያቄዎችን ቸል ማለቱ

ይሄው በዋል ስትሪት ጆርናል ይፋ የሆነው ሰነድ የፌስቡክ ሠራተኞች በተደጋጋሚ የሕገ ወጥ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎችን ብሎም በሰዎች የሚነግዱ ሰዎችን ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ቢጠይቁም የድርጅታቸው ምላሽ "ልል" መሆኑን ያጋልጣል።

እአአ በ2019 ቢቢሲ አረብኛ ተናጋሪ የቤት ሠራተኞች በኢንስታግራም ለሽያጭ እንደሚቀርቡ የሚያሳይ ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል። ታዲያ የፌስቡክ የውስጥ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ተቋሙ ይህንን ጉዳይ ቀደም ብሎ ያውቅ ነበር።

ዋል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው አፕ ስቶር ፌስቡክን ከገበያው እንደሚያስወጣ መዛቱን ተከትሎ ግን የተወሰነ እርምጃ ወስዷል።

ፌስቡክ ከ50 በላይ ቋንቋዎችን በመጠቀም የሰዎችን ደኅንነት የሚያስጠብቅ ስትራቴጂ እንዳለው በመግለጽ የቀረቡበትን ክሶች ለመከላከል ሞክሯል።

በተጨማሪም ትምህርታዊ የሆኑ ይዘቶችን እንደሚያዘጋጅ ብሎም በየአካባቢው ካሉ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች እና የእውነታ አረጋጋጮች ጋር እየሠራ እንደሆነም ገልጿል።

ተቺዎች እንደሚሉት ፌስቡክ ከ2̇.8 ቢሊዮን የሚበልጡ ተጠቃሚዎቹ የሚያጋሩትን ይዘት የሚከታተልበት መንገድ የለውም።

"ዘ ፌስቡክ ኢፌክት" የተሰኘው መጽሐፍ ጸሐፊ የሆኑት ዴቪድ ኪርክፓትሪክ "ፌስቡክ ከአሜሪካ ውጪ እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ለመቆጣጠር ምንም አይነት ተነሳሽነት የለውም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ነገር ግን ዋል ስትሪት ጆርናል ካጋራቸው መረጃዎች ቀልቤን የያዘው ፌስቡክ በ2020 ካካሄዳቸው የተዛቡ እና የሐሰት መረጃዎች ማጣራት ሥራ ውስጥ 13 በመቶው ብቻ ከአሜሪካ ውጪ የተደረጉ ናቸው" ሲሉም ባለሞያው ተናግረዋል።

"ይህ እንግዲህ 90 በመቶው ገበያው ከአሜሪካ ውጪ ያለ ድርጅት ነው" ብለዋል።

ከፌስቡክ ባለአክሲዮኖች ትልቅ ክስ ሊመሰረትበት መሆኑ

የፌስቡክ ባለአክሲዮኖች ውስብስብ ብሎም ትልቅ ክስ ሊመሰርቱበት መሆኑም ይፋ ከሆኑት መረጃዎች መካከል አንዱ ነው።

ባለአክሲዮኖቹ እንደሚሉት ፌስቡክ ከካምብሪጅ አናሌቲካ ቅሌት በኋላ ለአሜሪካ የንግድ ኮሚሽን የከፈለው የአምስት ቢሊዮን ዶላር ክፍያ ማርክ ዙከርበርግ በግሉ ከሚደርስበት የሕግ ኃላፊነት ለማስጣል የተደረገ ነው ሲሉ ይከሳሉ።

ፌስቡክ በሂደት ላይ ባለ የሕግ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም በማለት አልፎታል።

ፌስቡክ ራሱን የሚያሞግሱ ዘገባዎች የበለጠ ተደራሽነት እንዲኖራቸው አድርጓል?

በተገባደደው ሳምንት ኒው ዮርክ ታይምስ ይዞት የወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ፌስቡክ ገጽታውን ከፍ ለማድረግ በማሰብ ተቋሙ የሚያዘጋጃቸውን ይዘቶችን ግለሰቦች በሚመለከቷቸቀው ሰሌዳዎች ላይ (ኒውስ ፊድ) የመውሰድ አሠራር ዘርግቷል።

ጋዜጣው እንዳለው ይህ ፕሮጀክት "ሰዎች ስለ ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች አወንታዊ መረጃዎችን እንዲያገኙ ያለመ" ነው ሲልም ዘግቧል።

ፌስቡክ የኒውስ ፊድ ዝርዝሮቹን የሚመለከት ምንም አይነት ለውጥ አለማድረጉን ገልጿል።

የፌስቡክ ቃል አቀባይ ጆኤ ኦስቦርን በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩትም ይህ የመረጃ ክፍል በሦስት ከተሞች ብቻ የሚገኝ ብሎም ይዞት የሚወጣው መረጃም በግልጽ ከፌስቡክ የታተመ እንደሆነ የሚገልጽ መልዕክት የያዘ ነው ሲሉ ክሱን ተከላክለዋል።

ይህም እንደ ማንኛውም የማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች የሚታይ ነውም ብለዋል።

ፌስቡክ ኢንስታግራም ለታዳጊዎች "አደገኛ" እንደሆነ ያውቅ ነበር

ፌስቡክ ኢንስታግራም በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ታዳጊዎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና በተመለከተ ጥልቅ ጥናት ቢያደርግም ግኝቱን ይፋ አለማድረጉ ከፌስቡክ ፋይሎች ካመለጡ መረጃዎች መካከል አንዱ ነው።

ግኝቶቹም ኢንስታግራም ለታዳጊዎቹ "አደገኛ" ቦታ መሆኑን የሚያመለክት ይዘት እንደነበራቸው አትቷል።

ፌስቡክ ባካሄደው በዚህ ጥናት ላይ ከተሳተፉ ታዳጊ ሴቶች መካከል 32 በመቶው ኢንስታግራም ስለሰውነታቸው መጥፎ ስሜት እንዲሰማቸው እንደሚያደርገ መግለጻቸውን ዋል ስትሪት ይፋ አድርጓል።

ፎክስ ኒውስ እንዳለው የመረጃዎቹ አፈትላኪ ግለሰቦች ማንነታቸውን ይፋ ለማድረግ ብሎም ከአሜሪካ ኮንግረስ ጋር ለመተባበር ተስማምተዋል።