ሦስት የጂቡቲ እግር ኳስ ተጫዋቾች በፈረንሳይ ጥገኝነት ጠየቁ

ታትሟል

ሦስት የጂቡቲ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላት በፈረንሳይ ጥገኝነት የጠየቁ ሲሆን ከመካከላቸውም ለአንድ ሳምንት በአየር መንገድ ውስጥ የቆየው ተጫዋች በመጨረሻ መውጣት ችሏል።

ነስረዲን አብዲ የተሰኘው ይህ ተጫዋች በፓሪስ በኩል በ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞ ላይ ለመሳተፍ ሊሳፈር የሚገባውን አውሮፕላን በመተው እዚያው ጥገኝነት ጠይቋል።

ሁለቱ የቡድን አጋሮቹ ቢላል ሐሰን እና አቦቡካሪ ኤልሚ ረቡዕ ከአውሮፕላን ማረፊያው የወጡ ሲሆን ጉዳያቸውን ለፈረንሳይ መንግሥት እንዲያቀርቡ ሦስት ወር ተሰጥቷቸዋል።

ሦስቱም ተጫዋቾች በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ሳሉ በ72 ሰዓታት ውስጥ ጉዳያቸውን የሚያስረዳ ሰነድ እንዲያቀርቡ ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር።

ተጫዋቾቹን በማገዝ ላይ የሚገኘው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅትም ለጂቡቲ መንግሥት የሚሠሩት ሐሰን እና ኤልሚ ጥገኝነት ተከልክለው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ከተገደዱ እስር ቤት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳለው ገልጾ ነበር።

ኤልሚ በፖሊስ አገልግሎት ተቀጥሮ የሚሠራ ሲሆን፤ ሐሰን በጂቡቲ ሪፐብሊካን ዘብ ውስጥ በሚሠራበት ወቅት መፈጸም የማይፈልገውን ትዕዛዝ ለመከተል እንደሚገደድ ተናግሮ ጥገኝነት ጠይቋል ተብሏል።

"ትክክል ያልሆነ ነገር በተናገሩ ቁጥር በመንግሥት ይዋከባሉ" ሲሉ የጂቡቲ የሰብአዊ መብቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዣን-ሎፕ ሻል ተናግረዋል።

"ሐሰን የቤተሰቡን አባላት እንዲያስር ይገደድ ነበር። ይህንን እያደረገ ለመቀጠል አልፈለገም" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

የሁለቱም የትዳር አጋሮች አንዲሁም ቤተሰቦች በጂቡቲ ውስጥ ይገኛሉ ያሉት የማኅበሩ ፕሬዝዳንት የሐሰን ባለቤት በመጨረሻው የእርግዝናዋ ወራት ውስጥ እንደምትገኝም አስታውቀዋል።

ቡድኑ ከአራት ቀናት በፊት በአፍሪካ ሻምፒዮና በኒጀር 8 ለ 0 ተሸንፎ ከአልጄሪያ ወደ ሞሮኮ በቀጥታ መብረር ባለመቻሉ በፓሪስ አድርጎ ለመጓዝ ወደ ፈረንሳይ ተጉዞ ነበር።

ተጫዋቾቹ በቪዛ ብሎም በኮቪድ ሰነዶች መጓደል ምክንያት ከፓሪስ ወደ ሞሮኮ የሚሄደው በረራቸው አምልጧቸዋል። ቀጥሎም ጥገኝነት ስለሚጠይቁበት መንገድ እቅድ ማውጣታቸው ተነግሯል።

ሌሎች የቡድን አባላቶቻቸው ፓሪስን ለቀው ሲበሩ ሦስቱ የቡድን አባላት ግን ተደብቀው ቀርተዋል።

"በሰፊ የግብ ልዩነት ተሸንፈው ወደ አገራቸው መመለስ በጣም ፈርተዋል" ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ መሪ ተናግረዋል።

ከቀናት በፊት የፈረንሳይ ችሎት ሐሰን እና ኤልሚ ከአውሮፕላን ማረፊያው እንዲወጡ እስከሚፈቅድበት ጊዜ ድረስ ሦስቱም የእግር ኳስ ተጫዋቾች በጣቢያው ትራንዚት ዞን ውስጥ ቆይተዋል።

በምሽትም በዚያው በአየር ማረፊያው ውስጥ ባለ ሆቴል ውስጥ እንዲያርፉ ሲደረግ አንደነበረም ተገልጿል።

የተጫዋቾቹ ጥያቄ በፈንሳይ የስደተኞች ተቋም መልስ ካገኘ በፈረንሳይ ውስጥ እንዲኖሩ ሊፈቀድላቸው ይችላል። ቢቢሲ ከጂቡቲ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን መልስ ለማግኘት ሞክሮ ሳይሳካ ቀርቷል።