ዋሻ ቆፍረው ከእስር ቤት ካመለጡት ስድስት ፍልስጤማውያን አራቱ መያዛቸውን እስራኤል ገለጸች

ካመለጡት ስድስት ፍልስጤማውያን አራቱ መያዛቸውን እስራኤል ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በከፍተኛ ሁኔታ ጥበቃ ከሚደረግለት የእስራኤል እስር ቤት ካመለጡት ስድስት ፍልስጤማውያን መካከል አራቱን መልሳ እንደያዘች እስራኤል አስታወቀች።

እስራኤል መልሳ ከያዘቻቸው ፍልስጤማውያን መካከል ሁለቱ የተገኙት የመኪና ማቆሚያ አካባቢ ነው። ሌሎች ሁለቱ ደግሞ ናዝሬት ከተማ አካባቢ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።

ስድስቱ ፍልስጤማውያን ባለፈው ሰኞ ከእስር ቤት ካመለጡ በኋላ በፖሊሶች ሲፈለጉ ነበር።

በሰሜን እስራኤል ከሚገኘው ጊልቦዋ እስር ቤት ያመለጡት መሬት ሰርስረው ነበር።

ፍልስጤማውያን ከእሰራኤል ከእስር ቤት በዚህ መንገድ ካመለጡ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል።

እስራኤል የእስረኞቹ ማምለጥ ቢያስደነግጣትም፤ የፍልስጤም ታጣቂዎች ግን በተፈጠረው ነገር ኩራት ተሰምቷቸዋል።

ፍልስጤማውያኑ እስረኞች በእስር ቤቱ ውስጥ የሚገኘውን ክፍላቸውን ለወራት ቆፍረው እንዳመለጡ ተገልጿል።

በቆፈሩት ክፍተት ከሾለኩ በኋላ በድጋሚ ሌላ ትቦ ቆፍረው ከእስር ቤቱ ማምለጥ ችለዋል።

የደኅንነት ካሜራ ምስሎች እንደሚያሳዩት፤ እስረኞቹ ሰኞ ሌሊት ካመለጡ በኋላ መጥፋታቸው ታውቆ ፍለጋ የተጀመረው ንጋት አካባቢ ነበር።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የእስር ቤቱን የደኅንነት ክፍል ሲወቅሱ ተደምጧል። የእስር ቤቱን ንድፍ ያወጡት አርክቴክቶች ሳይቀሩ ስማቸው ሲነሳ ነበር።

ከዌስት ባንክ የተያዙና ከእስር ቤት የማምለጥ እድላቸው ሰፊ የሆነ ፍልስጤማውያንን በዚያ እስር ቤት ማቆየት ተገቢ አልነበረም የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል።

ፍልስጤማውያኑ ከቆፈሩት ከመሬት በታች በተላለፊያ ውጪ የሚገኝ የእስር ቤቱ መውጫ በር ላይ ለጥበቃ ተመድቦ የነበረው ሠራተኛ ተኝቶ ነበር የሚል ጭምጭምታ ቢኖርም እውነት መሆኑ አልተረጋገጠም።

እስራኤል በድጋሚ ከያዘቻቸው ፍልስጤማውያን እስረኞች አንዱ ዘካሪያ ዙቤይዲ ነው። እስራኤል ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች እጁ አለበት በሚል ተጠርጥሮ እአአ 2019 ላይ የታሰረው ዘካርያ የአል-አቅሳ ሰማዕታት ቡድን አመራር ነው።

የተቀሩት እስረኞች ሞሐመድ አርዳህ፣ ኤልሀም ካማጂ፣ ያኮብ ቃድሪ እና ሙናዲ ኢፋት ናቸው። የኢስላሚክ ጂሀድ ቡድን አባላት ሲሆኑ፤ እስራኤላውያን የሞቱበትን ጥቃት በማቀነባበር የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።