ስድስት ፍልስጤማውያን በቆፈሩት ዋሻ ከእስራኤል እስር ቤት አመለጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ስድስት ፍልስጤማውያን እስረኞች ጠንካራ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት ካመለጡ በኋላ እስረኞቹን አድኖ ለመያዝ እስራኤል ኦፕሬሽን ጀመረች።
ከእስር ቤቱ ያመለጡት እስረኞች ለወራት ያህል የእስር ቤት ክፍላቸውን ውጪ ካለ መንገድ ጋር የሚያገናኝ ዋሻ ለመሥራት ሲቆፍሩ ቆይተዋል ተብሏል።
እስረኞቹ ትናንት ለሊት ላይ ማምለጣቸው የተገለጸ ሲሆን፤ እስረኞቹ በእርሻ ስፍራ ሲሯሯጡ የተመለከቱ አርሶ አደሮች ለእስራኤል ባለሥልጣናት ጥቆማ አድርሰዋል።
ከእስር ካመለጡት መካከል አንዱ አል-አቅሳ የተባለ የታጣቂ ቡድን የቀድሞ መሪ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ የእስላማዊ ጂሃድ አባላት ናቸው።
የእስራኤል ማረሚያ ቤት አገልግሎት ኃላፊዎች የእስረኞቹን ማምለጥ፤ "ከፍተኛ የደኅንነት ውድቀት ነው" ሲሉት የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ደግሞ፤ "ጀግንነት" ሲሉ አወድሰዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ፍልስጤማውያኑ እስረኞች ተረዳድተው ከመጸዳጃ ክፍላቸው ጀምረው የቆፈሩት ዋሻ ከእስር ቤቱ ውጪ ካለ መንገድ ጋር የሚያገናኝ ነው።
የእስራኤል ደኅንነት ባለሙያዎች በእስር ቤቱ መጸዳጃ ክፍል ውስጥ እና መንገድ ዳር ያሉ ዋሻዎችን ሲመረምሩ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
ጄሩሳሌም ፖስት እንደዘገበው ከሆነ እስረኞቹ ዋሻውን ለመቆፈር ያረጀ ማንኪያ ተጠቅመዋል። የእስራኤል ደኅንነት ኤጀንሲ በበኩሉ እስረኞቹ ከእስር ቤቱ ውጪ ካለ አካል ድጋፍ ሳያገኙ አይቀርም ብሏል።
ተደብቆ በገባ ሞባይል ስልክ እስረኞቹ ውጪ ካለ አካል ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ እንደነበረ እና ከዋሻው ከወጡ በኋላ በመኪና እንደተወሰዱ ኤጀንሲው ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ከእስር ቤቱ ካመለጡት ስድስት እስረኞች አምስቱ በእስራኤል ላይ ከተፈጸመ ጥቃት ጋር በተያያዘ የእድሜ ልክ እስራት የተበየነባቸው ናቸው ሲል አስነብቧል።
ከእስር ቤቱ ያመለጡት እስረኞች ዌስት ባንክ አልያም ጆርዳን እንዳይገቡ የእስራኤል ፖሊስ መንገዶችን በመዝጋት ፍተሻ እያካሄደ ነው ተብሏል። ይሁን እንጂ ዌስት ባንክ እና ጆርዳን ከእስር ቤቱ 14 ኪሎ ሜትሮች ብቻ እንደሚርቁ ተመልክቷል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ናፍታሊ ቤኔት እስረኞቹን ለመያዝ የመላው እስራኤል የደኅንነት ኃይሎችን ትብብር የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
እስላሚክ ጂሃድ የእስረኞቹን ተግባር "ጀግንነት" ያለው ሲሆን፤ ጉዳዩ የእስራኤል መከላከያ ሥርዓትን የሚያስደነግጥ ነው ብሏል።
የሃማስ ቃል አቀባይ ፍውዚ ባርሁም ደግሞ "በጠላት እጅ የሚገኙ ታሳሪ ወንድሞቻችን ቆራጥነታቸው እንደማይከስም ያሳየ ትልቅ ድል ነው" ብለዋል።












