የሶማሊያ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ ተነገረ

ታትሟል

በሶማሊያ ባለሥልጣናት መካከል የተከሰተው አለመግባባት ሲጠበቅ የነበረውንና በቅርቡ ሊካሄድ የታቀደውን ምርጫ እንደማያስተጓጉለው ተነገረ።

ከፕሬዝዳንት ሞሐመድ ፋርማጆ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡት የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌ ናቸው የተፈጠረው አለመግባባት ለረጅም ጊዜ በተራዘመው የአገሪቱ ምርጫ ላይ ተጽእኖ አይኖረውም ሲሉ የተናገሩት።

"ምርጫው በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ ለማድረግ ቁርጠኛ ነን፤ ሌሎች ጉዳዮች በምርጫው ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ አይኖራቸውም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሮብሌ በጉብኝት ላይ ላለውና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ ለተመራ የልዑካን ቡድን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው ደብዛዋ የጠፋውን ሶማሊያዊት ሰላይ ጉዳይን መንግሥት በያዘበት መንገድ ምክንያት ነው።

በዚህም ሳቢያ በከፍተኛ ባለሥልጣናቱ መካከል በተፈጠረው ውዝግብ ሳቢያ ተራዝሞ በቆየው የምርጫ ሂደት ላይ እንቅፋት በመፍጠር ሊያስተጓጉለው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

በሶማሊያ የምክር ቤት አባላት ምርጫውን በመጪዎቹ የጥቅምትና የኅዳር ወራት ውስጥ ለማካሄድ ዕቅድ ተይዞለታል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አሚና ሞሐመድ እሁድ ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ እና ከፕሬዝዳንት ፋርማጆ ጋር ተገናኝተው በተከሰተው ችግር ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ ሁለቱም ወገኖች "ወደ ግጭትና ምርጫውን በድጋሚ ወደሌላ ጊዜ ከሚያስተላለፍ ወይም ተአማኒነቱን ከሚጎዳ" ማንኛውም እርምጃ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

የሶማሊያ ደቡባዊ ምዕራብ እና ጋልሙዱግ ክልል መሪዎች በፕሬዝዳነቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል የተፈጠረውን ፍጥጫ ለማርገብ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተነግሯል።

በፕሬዝዳንት ፋርማጆና በጠቅላይ ሚኒስትራቸው መካከል የተከሰተው አለመግባባት ተካሮ ወደ ግጭት ሊያመራና ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ሞቃዲሾ ውስጥ ተከሰተው አይነት ወታደራዊ ግጭት ሊከሰት ይችላል ተብሎ ተሰግቶ ነበር።