የግድያ ዛቻ የሚደርስባቸው ኢ-አማኒ የመብት ተሟጋቾች

ታትሟል

“አገኝሃለሁ፤ እገልሃለሁ፤ አንገትህን እቀላዋለሁ” ይህ ማስፈራሪያ የደረሰው ካናዳ የሚኖር የሶማሊያ ተወላጅ ነው፤ አያንሌ ይባላል።

‘ትሩ ሶማሊያ ፍሪደም ፔጅ’ ወይም እውነተኛ የሶማሊያ ነፃነት የተሰኘ የፌስቡክ ቡድን የመሠረተው አያንሌ እንዲህ አይነት ማስፈራሪያ ሲደርሰው የመጀመሪያው አይደለም። “ተላምጄዋለሁ” ይላል። ፌስቡክ ገፁን ያጨናቁት የእንገድልሃለን ዛቻዎች ናቸው።

የፌስቡክ ገፁ ታዋቂ ነው። ከ80 ሺህ በላይ አባሎች አሉት። አብዛኞቹ ሐይማኖት የላቸውም። እራሳቸውን “የቀድሞ ሙስሊሞች” ብለው ይጠራሉ።

ገፁ የተከፈተው ከሐይማኖት ጋር በተያያዘ ግልጽ ውይይቶችን እንዲደረጉ ነው። በተለይም በአብዛኛው የሶማሊያ ማኅበረሰብ ዘንድ ለተገለሉ የሶማሊያ ተወላጆች ነፃ መድረክ መስጠትን ግቡ አድርጓል።

ሙሉ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈቀደው አያንሌ የፌስቡክ ገፁ እንዴት እንደጀመረ እንዲያ ያወሳል. . .

እአአ 2016 ላይ አንድ የሶማሊያውያን የፌስቡክ ገፅ ተመለከተ። ሀሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርበት፣ ክርክር የሚካሄድበትም ገፅ ነበር።

“ልክ ስለ ሐይማኖት ማውራት ስጀምር ሁሉም ሰው ተቆጣ። ሰው የገደልኩ እስኪመስለኝ ድረስ።”

ወዲያው ከፌስቡክ ገፁ ተባረረ። ብዙ ጊዜ የሶማሊያ ተወላጆች በሚጀምሯቸው የውይይት ገፆች፤ ሐይማኖትን በተመለከተ ብዙሃኑ ከሚያምኑት ውጪ ሀሳብ ማንሳት አይደገፍም።

‘ነፃ መድረክ’

አያንሌ ከፌስቡክ ገፁ ሲባረር የራሱን ቡድን መሠረተ።

“ገፁ ሰዎች ያሻቸውን መናገር የሚችሉበት እንዲሆን እፈልጋለሁ” ይላል።

ዓመታት የዘለቀው የሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነትን ተከትሎ በማኅበረሰቡ ዘንድ ስለ ሐይማኖት መወያየት ክልክል እየሆነ እንደመጣ ያምናል።

“እስልምና አይነኬ ነው። ምንም አይነት ትችት መሰንዘር አይቻልም። አሁን ላይ ወጣቶች እየተቀየሩ ነው። በመጠኑም ቢሆን ለትችትና ለክርክር ክፍት ናቸው።”

አያንሌ እንደሚለው፤ ሶማሊያ አድገው በእርስ በእርስ ጦርነቱ ወቅትና ከዚያ በኋላም ወደ ምዕራባውያኑ አገራት ያቀኑ ሶማሊያውያን፤ አንድ ሰው ስለ እስልምና ክፉ ነገር ከተናገረ መገደል አለበት ብለው ያምናሉ።

እሱም ብዙ የሞት ማስፈራሪያ የደረሰው ለዚህ ነው። ሆኖም ግን ስለ ሐይማኖቱ መወያየት፣ መከራከር እንዲቻል ገፁን መክፈቱን ያስረዳል።

በሶማሊያ እና በሶማሊላንድም ከሐይማኖት ጋር የሚጻረር ንግግር ያሳስራል። የፌስቡክ ገፁ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ቆሟል።

አምና የዩኒቨርስቲ መምህሩ መሐሙድ ጃማ አህመድ ሀምዲ ሲታሰር በዚህ ገፅ ገንዘብ ተሰባስቧል። መምህሩ ድርቅን ለመከላከል መጸለይ ላይ ጥያቄ አንስቶ በፌስቡክ ገፁ በመጻፉ ነበር የታሰረው።

አስር ወር ከታሰረ በኋላ በይቅርታ ቢለቀቀም ለጥቃት ተጋላጭ ነው። አንድ ታዋቂ ኢማም ይገደል ብለዋል።

ይህ የሚያሳየው በሶማሊያም ይሁን በሶማሊላንድ በሐይማኖት መሪዎችና በመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ያለው መስመር እምብዛም አለመለያየቱን ነው።

የመጋለጥ ፍርሀት

በፌስቡክ ቡድኑ ኢ-አማኒዎች ብቻ ሳይሆን ክርስቲያኖች፣ ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች አሉ። ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሆነ ሲሰማቸው ፊታቸውን ወደ ገፁ ያዞራሉ።

እነዚህ ሰዎች እንጋለጥ ይሆን ብለው ይሰጋሉ። ጥቃት ወይም እስር ሊደርስባቸው እንደሚችልም ይፈራሉ። በፌስቡክ ገፁ ገንዘብ ይሰባሰባል። ስጋት ውስጥ ላሉ ሰዎች የአውሮፕላን ትኬት መግዣና የኑሮ ወጪ መሸፈኛም ይውላል።

ኬንያ ያለች ሶማሊያዊት ክርስቲያን ፌስቡክ ገፁ ላይ በስሟ አስተያየት ጽፋ ነበር። ማንነቷን ያወቁ ሰዎች ከታክሲ እያንገላቱ ሲያወርዷት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በሶማሊያ በስፋት ተሰራጭቷል።

የፌስቡክ ገፁ ከኬንያ እንድትወጣ ረድቷታል።

ሱዳን ውስጥ የሚኖር ሶማሊያዊ ፌስቡክ ላይ በጻፋቸው ትችቶች ሳቢያ በአክራሪ ሙስሊሞች ጥቃት እንደደረሰበት በመግለጽ የነአያንሌ ቡድን እንዲረዳው ጠይቆ ነበር።

ጥብቅ ምርመራ

መሰል የእርዱን ጥሪ የሚያቀርቡ ሰዎች ብዙ ስለሆኑ፤ ጥብቅ ምርመራ እንደሚያደርጉ ካሃ ዲህናን ትናገራለች።

ካሃ በኖርዌይ የሴቶች መብት ተሟጋች ናት። በፌስቡክ ገፁም ትታወቃለች።

“ምርመራ እናደርጋለን። የጎሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ስም እንጠይቃለን። ፌስቡክ ገፃቸው ላይ ጻፉትን አንብበን በእኛ ቡድን ውስጥ የሚያውቃቸው ሰው ካለ እንጠይቃለን። ብሔራቸውን ካልነገሩን እየዋሹ መሆኑን እናውቃለን” ትላለች።

ካሃ የግሏ የፌስቡክና የዩቲዩብ ገፅ አላት። የሶማሊያ ማኅበረሰብን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውይይት ታካሂዳለች።

‘የምትኖሪበትን አውቃለሁ’

የካሃ ዋና ግብ የሴቶችን ድምጽ ማስተጋባት ነው። እንደ አያንሌ እሷም ኢ-አማኒ ስለሆነች ማስፈራሪያ ይደርስባታል።

“በስለት እንገልሻለን ብለው ያስፈራሩኛል። የምትሞቺው በሙስሊሞች እጅ ነው ይሉኛል። አስፈራርተው ዝም ሊያሰኙኝ ይፈልጋሉ። አልፈራቸውም።”

የግድያ ዛቻ በሚያስከስስበት አገር መኖሯ ጠቅሟታል። ሶማሊያ ውስጥ ግን ግድያ፣ ጥቃት ቢደርስም ሳይመረመር ሊያልፍ ይችላል።

“ሲያስፈራሩኝ ከነበሩት ወንዶች ሁለቱ ትክክለኛ ስማቸውን ተጠቅመው ነበር ዛቻ ያደረሱብኝ። ታስረዋል።”

አያንሌም ሀሳቧን ይጋራል። ነገር ግን በርካታ ሶማሊያውያን ለጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን አይክደም።

“ገፁ ላይ ያሉት ብዙ ሶማሊያውያን ማንነታቸው እንዲታወቅ አይፈልጉም። ኢ-አማኒ ነን የሚሉት ለሕይወታቸው ይሰጋሉ” ይላል።

“ሰዎች ባሻቸው ነገር እንዲያምኑ እንፈልጋለን”

አያንሌ እና ካሃ ኢ-አማኒ ቢሆኑም ራሳቸውን ከሶማሊያ ማኅበረሰብ አላገለሉም።

“እንዲያውም ሶማሊያዊነቴ ጎልቶ ይሰማኛል። ትክክለኛ ማንነቴን አግኝቻለሁ” ትላለች ካሃ።

አያንሌ እንደሚለው፤ የፌስቡክ ገፃቸው አላማ ሙስሊሞችን ኢ-አማኒ ማድረግ አይደለም። ነገር ግን ከአንድ ሀሳብ ውጪ ሌላ አንሰማም የሚለው አመለካከት እንዲሸረሸር ይፈልጋል።

የማሰብ ነፃነት፣ የመናገር ነፃነት እንዲሰፍንም ይሻል።

“ገና ጅማሮ ላይ ነን። የጥቂቶችን ቀልብ ገዝተናል። ሰዎች ባሻቸው ነገር እንዲያምኑ፣ የመረጡትን አይነት ሰው እንዲሆኑም እንፈልጋለን።”