አፍጋኒስታን፡ ባይደን የጦሩን መውጣት ሲደግፉ ታሊባኖች አሸንፈናል አሉ

በሃሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሰዎችን በማስወጣት ሂደት ላይ የአሜሪካ ወታደር አንዲት ሕጻን ሰላምታ ስትሰጠው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ወታደሮችን ከአፍጋኒስታን የማስውጣት ውሳኔ ትክክል ነው በሚል አቋማቸው ጸንተዋል።

አሜሪካ ጦሯን ከአፍጋኒስታን ማስወጣቷ የታሊባን ታጣቂዎች ወደ ሥልጣን እንዲመለሱ ምክንያት ሆኗል።

ባይደን አሜሪካ ለ20 ዓመታት በአፍጋኒስታን የነበራት ቆይታ ካበቃ ከአንድ ቀን በኋላ ለአሜሪካዊያን ባደረጉት ንግግር ለረዥም ጊዜ መቆየት አማራጭ አልነበረም ብለዋል።

ከታሊባን አገዛዝ የሚሸሹ ከ120 ሺህ በላይ ሰዎችን ለማስወጣት የሠሩትን ወታደሮችንም አመስግነዋል።

እስላማዊ ታጣቂዎቹ ድል ማስመዝገባቸውን በመግለጽ ደስታቸውን ሲያከብሩ ቆይተዋል።

አሜሪካ መራሹ ጦር እአአ በ2001 ወደ አፍጋኒስታን የገባው ከመስከረም 11 ጥቃቶች በኋላ ታሊባንን ከሥልጣን ለማስለቀቅ የነበረ ሲሆን፤ ከጥቃቱ ጀርባ በእስያ አህጉር የተመሠረተው ታጣቂው ጂሃዳዊ ቡድን አልቃይዳ ጥፋተኛ ተብሎ ጣት ተቀስሮበታል።

በአሜሪካ ወታደሮች ለዓመታት የሰለጠኑት እና የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው የአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይሎች ድንገተኛ መፍረክረክ ምክንያት በሆነው የአሜሪካ ከአፍጋኒስታን መውጣት ባይደን በአገራቸው እና በአጋሮቿ በሰፊው ተተችተዋል።

የታሊባን ታጣቂዎች መላ አፍጋኒስታንን በ11 ቀናት እንደገና መቆጣጠር ችለዋል። ዋና መቀጫዋን ካቡልን ነሐሴ 15 በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካዊያንን፣ የአጋር አገራት ዜጎችን እና ለእነሱ ሲሠሩ የነበሩትን የአፍጋኒስታን ስደተኞችን ለማስወጣት አውሮፕላን ማረፊያውን እንዲቆጣጠሩ ወደ 6,000 የሚጠጉ ወታደሮችን አሰማርተዋል።

ከበረራዎቹ በአንዱ የመሳፈር ተስፋ ካለ በሚልም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በካቡል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተሰብስበዋል።

ባይደን ማክሰኞ ባደረጉት ንግግር በሥራው የተሳተፉትን ወታደሮችን አመስግነዋል። አፍጋኒስታን ያሉ እና ለመመለስ የሚፈልጉ አሜሪካውያንን ለማስወጣት ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም 200 ያህል አሜሪካዊያን በአፍጋኒስታን ይገኛሉ።

ፕሬዚደንት ባይደን በንግግራቸው ከአፍጋኒስታን ለመውጣት የተወሰደውን እርምጃ አጥብቀው ደግፈዋል።

ባይደን "ይህንን የዘላለም ጦርነት አላራዝምም። የዘላለም መውጫ ዘዴ አልዘረጋም። በአፍጋኒስታን ያለው ጦርነት አሁን አብቅቷል" ብለዋል።

አሜሪካ ራሷን ለመከላከል አፍጋኒስታን ላይ ወታደሮች አያስፈልጓትም ብለዋል ፕሬዚደንቱ።