በአሜሪካ የድሮን ጥቃት ስድስት ህጻናትን ጨምሮ አስር የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገደሉ

አሜሪካ አፍጋኒስታን ውስጥ አንድ አጥፍቶ ጠፊን ኢላማ አድርጋ በሰው አልባ አውሮፕላን [ድሮን] በፈጸመችው ጥቃት ስድስት ህጻናትን ጨምሮ አስር የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
አስሩ ሰዎች የተገደሉት ትናንት እሁድ ከቤታቸው አቅራቢያ ቆሞ የነበረ ተሽከርካሪ በፍንዳታ በተመታበት ወቅት ነው።
የአሜሪካ ሠራዊት እንዳለው መኪናው ኢላማ የተደረገው የአይኤስ የአፍጋኒስታን ቅርንጫፍ ተባባሪ የሆነ ቢያንስ አንድ ግለሰብ በውስጡ ስለነበረ ነው ብሏል።
ጨምሮም በመኪናው አቅራቢያ የነበሩ ሰዎች በጥቃቱ ተመትተው ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።
በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲሰሩ የነበሩና ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያስችል ቪዛ የነበራቸው ሰዎች ናቸው ተብሏል።
የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ከጥቃቱ በኋላ ስለተከሰተው ጉዳት ምርመራ እያደረገ መሆኑን ነገር ግን 10 ሰዎች እንዴት ሊገደሉ እንደቻሉ ግልጽ አይደለም ብሏል።
ዕዙ ባወጣው መግለጫ ላይም በሰው አልባ አውሮፕላን አማካይነት ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በርካታ "ከባድና ተከታታይ ፍንዳታዎች" እንደነበሩ አመልክቷል።
"በመኪናው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የሚፈነዱ ቁሶች ነበሩ፤ ይህም ተጨማሪ ጉዳትን አስከትሎ ሊሆን ይችላል" በማለትም ግምቱን ገልጿል።
ማዕከላዊው ዕዝ ቀደም ሲል በአፍጋን ያለው የአይኤስ ቅርንጫፍ በካቡል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ደቅኖት የነበረውን "እርግጠኛ ጥቃት" በማስወገድ በኩል የተሳካ ነበር ብሎ ነበር።
ባለፈው ሐሙስ ከካቡል አየር ማረፊያ ውጪ ተፈጽሞ 13 የአሜሪካ ወታደሮችን ጨምሮ ከ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን የገደለውና የአይኤስ ቅርንጫፍ የሆነው ቡድን ኃላፊነቱን የወሰደው የቦምብ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ አሜሪካ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ትገኛለች።
በጥቃቱ የተገደሉት በርካታዎቹ ሰዎች ካቡል በታሊባን ኃይሎች ቁጥጥር ስር መውደቋን ተከትሎ ከአገሪቱ ለመውጣት ተስፋ አድርገው ሲጠባበቁ የነበሩ ናቸው።
ዛሬ ሰኞ አንድ ባለሥልጣን ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት በዋና ከተማዋ ካቡል ውስጥ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የተተኮሱ ሮኬቶች በአሜሪካ ፀረ ሚሳኤል መከላከያ እንዲመክኑ ተደርገዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እንዳለው ጆ ባይደን ስለተፈጸመው የሮኬት ጥቃት ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
በተፈጸመው የሮኬት ጥቃት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም።
አሜሪካ አየር ማረፊያውን ከተጨማሪ ጥቃቶች ለመከላከል ፀረ ሮኬትና ሞርታር መከላከያ ሥርዓት መዘርጋቷ ተነግሯል።
ከአፍጋኒስታን የሚወጡ ሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ ነጻ ቀጠና ካቡል ውስጥ እንዲኖር የሚያስችል የውሳኔ ሐሳብ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በፈረንሳይና በብሪታኒያ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

















